
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ተገኝተው የአርሶ አደሮችን የሰብል ልማት እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ ኀላፊ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎችም የዞን እና የክልል ከፍተኛ መሪዎችም ተገኝተዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በሩዝ ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የኾነውን የፎገራ አካባቢ ታታሪ አርሶ አደሮችን በአካል ተገኝተን ለማበረታታት ነው ብለዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች በሩዝ ምርት ላይ ተግተው እየሠሩ ነው፤ እንደ ሀገር የተያዘውን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ተልዕኮን ለማሳካትም ትልቅ አቅም ናቸው ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በፎገራ ወረዳ የተመለከቱት የሩዝ ሰብል ቁመና እንደ ክልል 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በቂ ማሳያ ነው ብለዋል። ከሰሞኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በአርሶ አደሮች ቀየ ጭምር እየተዘዋወሩ የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ እንደኾነም ገልጸዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ።
አርሶ አደሮች የቀረበላቸውን ግብዓት በአግባቡ ተጠቅመው አጥጋቢ ሰብል ማምረታቸውን ስለመመልከታቸውም አንስተዋል። ይህም “የአማራ ክልል ሕዝብ የገጠሙትን ችግሮች ተሻግሮ ለሰላም እና ለሀገራችን ልዕልና መረጋገጥ መሠረት እየኾነ መምጣቱን ማሳያ ነው” ብለዋል።
በዛሬው ምልከታቸው የፎገራ አርሶ አደሮች የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ በሩዝ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መኾኑን አይተናል ነው ያሉት።
ሙሉ ጊዜያቸውን በልማት ላይ በማሳለፍ ለራሳቸው እና ለሀገር እድገት ለሚሠሩ አርሶ አደሮች በሙሉ ምስጋና ይገባልም ብለዋል ዶክተር አብዱ ሁሴን። ይህንን ውጤት አስጠብቆ ለመቀጠል ሰላም የማይተካ ሚና እንዳለውም አስምረውበታል።
አርሶ አደሮች ሁሉንም ነገር በሰላም የሚፈቱበት ብልሃት አላቸው፤ የካበተ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎቻቸውን በመጠቀም የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅ እና በሙሉ አቅም ወደ ልማት መግባት አለባቸው በማለት አሳስበዋል።
ከያዝነው የምርት ዘመን በበለጠ ቀጣዩን የምርት ዘመንም በምርት እና ምርታማነት የታጀበ እንዲኾን በቂ ግብዓት የማቅረቡ እንቅስቃሴ ከወዲሁ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!