
ደሴ: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ከሁለት ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ለመሥጠት አቅዶ እየሠራ ነው። በዓለማችን 51 በመቶ የሚኾነው ዓይነ ስውርነት የሚከሰተው በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት መኾኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በዚሁ በሽታ ምክንያትም 49.9 በመቶ ያህል ኢትዮጵያዊያን ለዓይነ ስውርነት እንደሚዳረጉ በቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሐኪም እና በሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኀላፊ እንዳልካቸው ያረጋል ተናግረዋል። በአብዛኛው በዕድሜ መግፋት የሚከሰተውን የዓይን ሞራ ግርዶሽ ለመከላከል “ኪውር ብላይንድነስ” ከሚባል ተቋም ጋር በመተባበር ከሁለት ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ለመስጠት አቅደው እየሠሩ መኾኑን የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ ተበጀ ገልጸዋል።
እስካኹንም ከ330 በላይ ወገኖች ታክመው የዓይን ብርሃናቸው እንደ ተመለሰላቸውም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል። በቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ሲታከሙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ትርንጎ አበበ፣ አባ ዳመና ቁምነሳ፣ አሰፋ አልዬ እና ወይዘሮ ሉባባ ሰይድ የዓይን ብርሃናቸውን በማጣታቸው ለበርካታ ችግሮች ተዳርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አኹን ላይ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውንም ገልጸዋል። “በመታከማችን እይታችን ብቻ ሳይኾን የመኖር፣ የመሥራት እና የመለወጥ ተስፋችንም ተመልሷ” ብለዋል። የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ኀላፊው እንዳልካቸው ያረጋል እንዳሉት እስካኹን በ13 ዙር ከ20 ሺህ በላይ የሚኾኑ ወገኖች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ማግኘታቸውን አግኝተዋል።
በዚህ ዙር እስከ 3 ሺህ ለሚደርሱ ወገኖች ሕክምና ለመስጠት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ለሕክምናው ስኬታማነት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እና የሰው ሃይል መሟላቱንም ኀላፊው አስረድተዋል። የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ያገኙ ወገኖች በሐኪሞች የተሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ እንደሚተገብሩም አሳስበዋል።
የኪውር ብላይንድነስ ፕሮጀክት የአድቮኬሲ ፣ ግምገማና ክትትል ሥራ አሥኪያጅ ሀገሩ ከበደ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት የሚከሰትን ዓይነ ስውርነት ለማስቀረት በመላ ሃገሪቱ ከሚገኙ 25 ሆስፒታሎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን አስታውሰዋል። ከቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ጋር በመሥራታቸው በርካቶችን ከስቃይ ማላቀቅ መቻላቸውን ተናግረዋል። አቶ አገሩ ለሥራው ስኬት የሚያግዙ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከ20 ሺህ በላይ የሚኾኑ ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂ መኾናቸውን የገለጹት የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ ተበጀ ናቸው። በሽታው በሕክምና የሚድን በመኾኑ ኅብረተሰቡ ወደ ሆስፒታሉ መጥቶ በነጻ እንዲታከም ጥሪ አቅርበዋል።
ከኅዳር 14 እስከ ኀዳር 20 ድረስ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ላለባቸው ወገኖች ሕክምና እንደሚሰጡም የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጅ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!