ኅዳር ሲታጠን

49
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ስፓኒሽ ፍሉ’ የተሰኘ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር። ‘የወረርሽኞች ሁሉ “እናት” በሚል የሚጠራው ይህ ወረርሽኝ በሁለት ዓመት ብቻ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ሕይዎት ቀጥፏል። ያኔ የዓለም ሕዝብ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ነበር። ከሕዝቡ አንድ ሦስተኛው በወረርሽኙ ተይዞ እንደነበር ተመራማሪዎች እና የታሪክ አጥኚዎች ይናገራሉ። ወረርሽኙ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በላይ ሰዎችን ገድሏል ነው የሚባለው። ያኔ ሳይንስ እንደ ዛሬው አልተራቀቀም ነበር። በሽታ መከላከልም ቀላል አልነበረም።
ሐኪሞች ‘የኅዳር በሽታ’ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ቢያውቁም፤ የበሽታው መንስዔ ባክቴሪያ እንጂ ቫይረስ መኾኑን አልተገነዘቡም ነበር።
ያኔ ዓለም አቀፍ የጤና ሥርዓት ማዕቀፍም አልነበረም። ሃብታም በሚባሉ ሀገራት ሳይቀር የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ እንደ ቅንጦት ይቆጠር ነበር።
‘ስፓኒሽ ፍሉ ዓለምን እንዴት ለወጠ’ በሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ፔል ራይደር ያኔ ኢንዱስትሪ በተስፋፋባቸው ሀገራት ሐኪሞች የእራሳቸው ቅጥረኛ ነበሩ ይላሉ። ሐኪሞች በተራድኦ ድርጅቶች ወይም በሃይማኖት ተቋሞችም ይደገፉ ነበር።
‘የኅዳር በሽታ’ ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነበር ጉዳት ያስከተለው። በብዛት የሞቱት ከ20 እስከ 40 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ናቸው።
ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የተመለሱ ወታደሮች ይኖሩበት በነበረ ማቆያ ውስጥ እንደተቀሰቀሰ የሚታመነው ይህ ወረርሽኝ፤ በዋነኛነት ያጠቃው ወንዶችን ነበር። ድሃ ሀገሮችም በግንባር ቀደምነት ተጎድተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አፍሪካ ትጠቀሳለች፡፡
የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በኢትየጵያ ከኅዳር 7 እስከ ሕዳር 20 ቀን 1911 ዓ.ም ለ14 ቀናት ገደማ የቆየ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በሽታው በኅዳር ወር የተከሰተ በመኾኑ ሕዝቡ የኅዳር በሽታ እያለ ጠራው:፡
ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ወረርሽኙ እስከ 40 ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጓል ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 9 ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል ብለዋል በመጽሐፋቸው፡፡ በተለይም በዚህ ሳምንት ሕዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመኾኑ በቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደ ባሕል ተወስዶ በየዓመቱ ሕዳር 12 ቀን የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር፤ ይህም በተለምዶ ሕዳር ሲታጠን በሚልም እየተጠራ እስከዛሬ ዘለቀ፡፡
👉የድንቅነሽ ግኝት
ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ልክ በዚህ ሳምንት ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም በአፋር ክልል ውስጥ ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የኖረችውን የሉሲ ድንቅነሽ አጽሟ የተገኘችበት ቀን ነበር። በኢትዮጵያ በአፋር የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በዶናልድ ጆንሰን የሚመራው የሳይንስ ሊቃውንት በጎርጎሪያኑ 1974 ቅሪተ አካላትን በማሰስ ላይ ነበሩ።
በዚሁ ዓመት ኅዳር ወር ታዲያ ተመራማሪዎቹ በቁፋሮ ያወጧቸው ከነበሩ ቁርጥራጭ ቅሬተ አካሎች እና የመገለገያ መሣሪያዎች በተለየ ሁኔታ በብዛትም በመጠኑም ከፍ ያለ እና ለምርምራቸው ፍንጭ የሚሰጥ ቅሬተ አካል በቁፋሮ አገኙ። በበረሃማው የአፋር ዝቅተኛ ቦታ ሐዳር ላይ በጣሉት ድንኳን ውስጥ ሊቃውንቱ ይህ ግኝት የፈጠረባቸውን ደስታ ያከበሩት ግን እንዲሁ አልነበረም።
በዚያን ዘመን በገነኑት ዘቢትልስ በተባሉ ሙዚቀኞች የተቀነቀነውን “ሉሲ ኢን ዘስካይ ዊዝ ዘ ዲያመንድ” በሚለው ሙዚቃ አጅበው ነበር።
እናም ይህ ሚሊዮን ዓመታትን የተሻገረ ቅሪተ አካል ስያሜ ከዚህ ሙዚቃ ጋር ተቆራኘ። ኢትዮጵያዊ ስያሜዋ ግን ድንቅነሽ ኾነ። ሉሲ ወይም በኢትዮጵያዊ ስሟ ድንቅነሽ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታትን ተሻግራ የኖረች በመካከለኛ ዕድሜ ያለች ሴት መኾኗንም ተመራማሪዎቹ ለዓለም ይፋ አደረጉ።
ከዚህ ባሻገር ቅድመ አያቶቻችን ቢያንስ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በሁለት እግራቸው መራመድ ይችሉ እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው በሉሲ አስደናቂ ግኝት ነው።
የሉሲ ቅሬተ አካል የዚያን ዘመን ሰው ይራመድ እንደነበር አሳይቷል፡፡ በአሜሪካው ክሊቭላንድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት በኾኑት ዶናልድ ጆንሰን የተገኘው የሉሲ ቅሬተ አካል አውስትራሎፒቲከስ ከሚባለው ቀደምት ዝርያ የሚመደብ ኾኖ ተገኝቷል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ሉሲ 27 ኪሎ ግራም ክብደት እና 1 ነጥብ 1 ሜትር ቁመት አላት።
ነገር ግን የዳሌ እና የእግር አጥንቶቿ ከዘመናዊው ሰው ተመሳሳይነት ያላቸው በመኾኑ የሉሲ ዝርያዎች ቀጥ ብለው መቆም እና መራመድ የሚችሉ መኾናቸውን ተረጋግጧል።
የሉሲ መገኘት ወደ ኋላ በኢትዮጵያ ለተጘኑት እንደ «አርዲ» እና «ሰላም» ያሉ ቅሬተ-አካላት መሠረት ጥሏል።
👉የጀርመን የመጀመሪያዋ መራሂተ መንግሥት
አንጌላ ሜርክል የጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት መራሂተ መንግሥት ኾነው የተሾሙት ኅዳር 13 ቀን 1998 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር።
ሜርክል ለ16 ዓመታት ያህል የጀርመን መራሂተ መንግሥት ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተው ለ16 ዓመታት አገልግለው በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ሥልጣናቸውን ለኦላፍ ሾልዝ ለቅቀዋል።
በአውሮፓ ውስጥ ከሩሲያ በመቀጠል በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የኾነችውን ጀርመን ያሥተዳደሩት ሜርክል ሀገራቸው የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር ውስጥ ጠንካራዋ ደጋፊ እንድትኾንም አስችለዋል፡፡
ሀገራቸው ጀርመን ስደተኞችን ተቀብላ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለባት በሚል ጠንካራ አቋም የነበራቸው ሜርክል በዚህም በሀገራቸው በሚኖሩ ሌሎች ዜጎች በጥሩ ዕይታ እንዲታዩም አስችሏቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰበቡም በሥልጣን ዘመናቸው በመልካም የሚታዩ ሰውም ናቸው፡፡
ሜርክል በዓለም ላይ ጦርነቶች እንዳይቀሰቀሱ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውም ይነገራል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሠው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ሀጋራቸው ቀድማ መድረስ አለባት በሚል እሳቤ የሚታወቁት የጀርመን የመጀመሪያዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርከል ይህንንም በተግባር ስለመፈጸማቸው ነው ያስረዱት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ👇https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው “የእንደራሴው ፍኖት” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በደቡብ ጎንደር ዞን የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ ነው።