
ጎንደር: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሑራን የተዘጋጀው “የእንደራሴው ፍኖት” የተሰኘው እና ለሀገራቸው እና ለጎንደር አካባቢ ትልቅ አበርክቶ ባላቸው አቶ ባዩህ በዛብህ የሕይዎት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሐፍ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በተገኙበት ተመርቋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ ባዩህ በዛብህ በኖሩባቸው ዘመናት ለሀገር በሚጠቅሙ ኀላፊነቶች ላይ ተሰማርተው ጉልህ አስተዋጽኦ አብርክተዋል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የዘመናችን ጀግና መኾናቸውን ምስክርነት የሚሰጠው እና በርሳቸው ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው መጽሐፍ በሚመረቅበት ዕለት በመገኘቴ ደስ ይለኛል ነው ያሉት፡፡
አቶ ባዩህ በዛብህ በደምቢያ ቆላድባ በመምሕርነት፤ በንጉሠ ነገሥቱ ፓርላማ የደምቢያ ሕዝብ እንደራሴነት፤ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኝነት፤ በጎንደር ክፍለ ሀገር መልሶ ማቋቋም እና ልማት ማኅበር (ጎልማ) መሥራች እና አመራርነት፤ በጎንደር ሰላም እና ልማት ሸንጎ አመራርነት፤ በአሥተዳደር ወሰን እና ማንነት ኮሚሽን አባልነት፤ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ኮሚሽን አባልነት እንዲሁም ሌሎች ኀላፊነቶች ላይ ተመድበው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በዕውቀት እና በብልሀት ሀገራቸውን አገልግለዋል ብለዋል፡፡
ጎንደር የአቶ ባዩህ ከልጅነት እስከ አሁን ድረስ ግልጋሎት አልተለያትም ያሉት ዶክተር አስራት ለልማቷ እና ለሰላሟ መታገላቸውን ገልጸዋል፡፡
“የእንደራሴው ፍኖት” የተሰኘው መጽሐፍ የአቶ ባዩህ የሕይዎት ታሪክ ብቻ እንዳልኾነ የገለጹት ዶክተር አስራት አጸደ ወይን በሦስት መንግሥታት ውስጥ ሀገርን እና ሕዝብን በጨረፍታ የሚያስቃኝ የታሪክ ሰነድ ነው ብለዋል፡፡
በየዘርፉ ላሉ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ተራማጅ እና ገንቢ አቅጣጫ የሚሰጥ የአንድ ብቁ እንደራሴ፤ መምህር፤ ዳኛ፤ ሀገር አገልጋይ እና አባትን መልዕክት የያዘ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የዚህ መጽሐፍ መዘጋጀት በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ሲኾን ለተቋሙ ስኬት፤ ለአቻ ተቋማት ደግሞ ምሳሌ ይኾናል ብለዋል ዶክተር አስራት፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛዉ አቶ ባዩህ ደፋር እና አይነኬ የሚባሉ ጉዳዮችን በመድፈር የሚታወቁ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ባሕሪያቸውም ከልጅነት እስከ ዕውቀት የቀጠለ ነው ብለዋል፡፡
የአቶ ባዩህ ታሪክ በመጽሐፍ መልክ በመዘጋጀቱ ለቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅም መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለጎንደር ሰላም እና ልማት ደከመኝ ሳይሉ እየሠሩ የሚገኙ ሰው መኾናቸውንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡
ለልጆች የሚነገር ታሪክ ማስቀመጥ ተገቢ በመኾኑ ጎንደር ዩንቨርሲቲ ታሪክን ሰንዶ ለማስቀመጥ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
መጽሐፉ የተጻፈላቸው አቶ ባዩህ በዛብህ በታሪካቸው ዙሪያ በተጻፈው መጽሐፍ መደሰታቸውን ገልጸው መጽሐፉ የሳቸው ታሪክ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ብለዋል፡፡
ታሪክን ሰዎች ከሞቱ በኋላ ለመፈለግ ከመድከም ግለሰቦች በሕይዎት እያሉ ማጥናት እና በመጽሐፍ መልክ ማስቀረት አስፈላጊ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ በተሠራው ሥራም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሊመሠገን ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ሁሉ የታሪክ ሰነድ ባለቤታቸው ወይዘሮ ዘርፊቱ አርዓያ እገዛ እንደነበረውም አቶ ባዩህ ገልጸዋል፡፡
የ48 ዓመታት የጋብቻ ታሪክ በአደባባይ መገለጹ እንዳስደሰታቸውም የአቶ ባዩህ ባለቤት ወይዘሮ ዘርፊቱ አርዓያ ገልጸዋል፡፡
ታሪኩ ለትውልድ አስተማሪ እንደሚኾን የገለጹት ወይዘሮ ዘርፊቱ አቶ ባዩህ በሂዎት ዘመናቸው በማኅበረሰቡ፣ በቤተሰብ እና በሥራ ባልደረቦቻቸው ተወዳጅ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለአሚኮ ከሰጡ ተሳታፊዎች አገኘሁ ተስፋ (ዶ.ር) እና ወይዘሮ አስካል አበጋዝ የአቶ ባዩህ በዛብህ መጽሐፍ አሁን ያለውን እና ቀጣዩን ትውልድ በሚገባ ማስተማር የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገር ሰላም፣ አንድነት እና ልማት ያበረከቱ ግለሰቦችን ታሪክ ማስቀመጥ እና መሰነድ ተገቢ ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ የአቶ ባዩህ የሕይዎት ታሪክ መሰነዱ ለሀገር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!