በደሴ ከተማ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ፡፡

77

ደሴ: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው ኳሊቲ ማኛ ጤፍ የዱቄት ፋብሪካ ተመርቆ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡

በፋብሪካው የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመኾናቸው በኑሯቸው ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለማሥተዳደር እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ እንደሚያስችላቸውም ነው ያብራሩት፡፡

የኳሊቲ ማኛ ጤፍ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አይቸው በለጠ ፋብሪካው ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው በቀን እስከ 400 ኩንታል ዱቄት እንደሚያመርትም ገልጸዋል፡፡ ግብዓትን ከአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚጠቀም ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለ20 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን እና በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር እስከ 50 ሰው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አለባቸው ሰይድ በበጀት ዓመቱ እስከ 75 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የአንቨስትመንት ጥያቄ ለመመለስ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ፋብሪካው ከአርሶ አደሮች ምርት በመቀበል የሚያመርት በመኾኑ ለአካባቢው አርሶ አደሮች እና ነዋሪዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ሌሎች ፋብሪካዎች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ማምረት ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ከተማ አሥተዳደሩ የከተማውን ሰላም በማረጋገጡ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

መሬት በማቅረብ፣ ብድር በማመቻቸት እንዲሁም የመብራት እና የሌሎች መሠረተ ልማቶችን የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰይድ አብዱ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የትብብር መድረክ መቋቋሙ የፍትሕ ሂደቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ እንደሚያደርገው ተጠቆመ።
Next articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው “የእንደራሴው ፍኖት” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ፡፡