የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የትብብር መድረክ መቋቋሙ የፍትሕ ሂደቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ እንደሚያደርገው ተጠቆመ።

30

ደባርቅ: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዳኝነት እና ፍትሕ ተቋማት የምክክር መድረክ በደባርቅ ከተማ ተካሂዷል።

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የፍትሕ ተቋማት ሚና ጉልህ ነው። የፍትሕ ተቋማቱ ሥራቸውን በተሻለ መንገድ እንዲሠሩ የትብብር እና የምክክር መድረክ መቋቋሙም ወሳኝ ነው።

በጋራ መድረኩ የፍትሕ ተቋማት፣ ፖሊስ መምሪያ፣ ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በጋራ እየተሳተፉ ነው። በምክክር መድረኩ ላይ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ ተገኝተዋል።

የፍትሕ መምሪያው ኀላፊ እና የጋራ መድረኩ ምክትል ሠብሣቢ ነጋ ሲሳይ “ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ የግል ተበዳዮች በፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይ እንደ አንድ ተዋናይ የሚወሰዱ በመኾናቸው ተፈላጊውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል” ብለዋል።

ኀላፊው የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የትብብር መድረክ መቋቋሙ ማኅበረሰቡን እና የፍትሕ ተቋማቱን ለማቀራረብ ከማስቻሉም በላይ የፍትሕ ሂደቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ፍትሕን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የብዙ አጋር ተቋማትን ትብብር የሚጠይቅ በመኾኑ ተቋማቱ ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ለማስቻል የተደረገው የተቋማዊ የአሠራር ለውጥ እና የጋራ መድረኩ ወሳኝነት አለው ሲሉ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ግዛቸው ሙጨ ተናግረዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የምርመራ ዋና ክፍል ኀላፊ ኢንስፔክተር ያይኔ አስማማው የፖሊስ ሥራ ወንጀል እንዳይፈፀም ቀድሞ መከላከል ሲኾን ከተፈፀመም በኋላ ወንጀለኛውን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ይሠራል ብለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ተቀናጅቶ ሕግን ማስፈፀም መቻል ውጤት አለው ሲሉ ነው ለአሚኮ የተናገሩት።

የሰሜን ጎንደር ዞን የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ባንችአምላክ መልካሙ በዞኑ የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ኀላፊዋ በቀጣይ ከፍትሕ ተቋማቱ ጋር በጋራ መሥራት መቻሉ ችግሩን ለመቀነስ ብሎም ለመቅረፍ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

መድረኩ በቀጣይ ጊዜያት የኅብረተሰቡን ንቃተ ሕግ ለማሻሻል እንደሚሠራ ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታል የግንባታ ሂደት የጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱ ከሪም መንግሥቱ ጎበኙ።
Next articleበደሴ ከተማ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ፡፡