
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ሠልጣኞችን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አሥተላልፈዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት ትምህርት የሰውን ልጅ ዕውቀት እና ክህሎት የማሳደግ አቅሙ የማይተካ መኾኑ የአደጉ ሀገራት ማሳያዎች ናቸው።
የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩትም ከተመሠረተ ጀምሮ በክልሉ ይታዩ የነበሩ የአገልግሎት ውጤታማነት እና ቅልጥፍና ችግሮችን በመፍታት እና ተቋማት በሠለጠነ የሰው ኀይል እንዲመሩ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ሠልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ደረጃን ከማሻሻል ባለፈ ሀገር ለምትፈልገው ኀላፊነት ብቁ መኾን እና ትውልድ የሚፈልገውን ሥራ ማከናወን የሚያስችል አቅም መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።
ሀገሪቱ የምትፈልገውን ትክክለኛ ጥያቄ በመመርመር እያጋጠሙ ያሉ እና በቀጣይም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመተንበይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንደሚገባም አስረድተዋል።
‘ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ’ ከሚል እሳቤ በመውጣት ‘እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት’ የሚል ትውልድ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
ሠልጣኞች በትምህርት ቆይታቸው ባገኙት ዕውቀት እና ልምድ ተጠቅመው አሁን ላይ በክልሉ እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች የመፍትሄ አካል እንዲኾኑም ጠይቀዋል። ኢንስቲትዩቱ እያከናወነ ለሚገኘው ሥራም የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ኢንስቲትዩቱ በፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በፐብሊክ ፖሊሲ እና አመራር እንዲሁም በፖለቲካል ኢኮኖሚ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን 222 ሠልጣኞች አስመርቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!