
አዲስ አበባ: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራሮች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ በኩታ ገጠም እየለማ ያለን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ የባሌ ዞን በግብርና ልማት የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ናት ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል ስንዴን በስፋት በማልማት ከፍተኛውን ድርሻ ከሚወስዱ አካባቢዎች አንዱ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የመንግሥት የአምስት ዓመት የልማት ስትራቴጅ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ በማልማት የራስን የምግብ ፍጆታ ማረጋገጥ መኾኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ስንዴን ከራስ አልፎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የተቻለበትን አቅም መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር፣ የእርሻ ትራክተር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ከመጠቀም በተጨማሪ አርሶ አደሮችን በማደራጀት እና በኩታ ገጠም በማልማት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንም አንስተዋል።
በቀጣይ የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታን ከማረጋገጥ ባለፈ “አርሶ አደሮች የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲያደርጉ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚታቸውን እንያሳድጉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ጥረት ይደረጋል” ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ድኤታው አምራች አርሶ አደሮች ስንዴን በብዛት እና በጥራት በማምረት ምርቱን ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ፋብሪካዎችን በማቋቋም የስንዴ ዱቄት እንዲያመርቱ ይደረጋል።
ይህን ከግብ ለማድረስ አምራቾችን በፋይናንስ፣ በግብዓት እና በሥልጠና ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ቴወድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!