ሰልጣኞች በተመረቁበት የሙያ መስክ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

48

ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።

የኢንስቲትዩቱ ፕሬዚዳንት እሱባለው መሠለ እንዳሉት በኢንስቲትዩቱ አጫጭር ሥልጠናዎችን፣ መደበኛ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቶችን እያስተማረ ይገኛል፤ ምርምሮችንም ያካሂዳል ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የትምህርት መርሐ ግብሮች ከተጀመሩ አንስቶ በተቋሙ ሥም 11 የምርምር ውጤቶች በዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ታትመዋል ነው ያሉት። እነዚህ የምርምር ውጤቶች ለሥልጠናው ዋና ግብዓት እንዲኾኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የተጀመሩት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ድግሪ መርሐ ግብሮች ዋና ዓላማ የተቋሙ የምርምር እና ሥልጠና ሥራዎች እንዲዘምኑ እና ክልሉን በሰው ኃይል አቅም ለማሳደግ ታስቦ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ታሪክ፣ ወግ፣ ባሕል እንዲሁም የሚታዩ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው የሚሰነዱበት እና የሚተለሙበት ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር እንዲቻል ኢንስቲትዩቱን ወደ አማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከወኑ መኾኑንም ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹም በሠለጠኑበት ዘርፍ በታማኝነት እንዲያገለግሉ እና አሁን ላይ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም መደፍረስ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ባለድርሻ አካላትም ለክልሉ ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ትኩረት እንዲያደርጉ እና ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጃናሞራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የኤክስሬይ የሕክምና መሣሪያ ድጋፍ ተደረገለት፡፡
Next articleከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አልሞ እየሠራ መኾኑን የባሌ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።