የጃናሞራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የኤክስሬይ የሕክምና መሣሪያ ድጋፍ ተደረገለት፡፡

59

ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር እና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ለጃናሞራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የኤክስሬይ የሕክምና መሣሪያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የጃናሞራ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ለጃናሞራ እና ለበየዳ ወረዳ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ነው።

ሆስፒታሉ በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በኤክስሬይ ላብራቶሪ መሣሪያ እና ሌሎች ችግሮች ለማኅበረሰቡ አስፈላጊውን የሕክምና ግልጋሎት ለመስጠት ሲቸገር ቆይቷል።

በተለይ በኤክስሬይ ላብራቶሪ መሣሪያ መታየት ያለባቸው ሕሙማን ሲኖሩ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ደባርቅ እና ጎንደር ከተማ ለመታየት ይገደዱ ስለነበር ብዙዎች ለከፍተኛ እንግልት እና ወጭ ሲዳርጉ ቆይተዋል።

ሆስፒታሉ ያለበትን መሠረታዊ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባትም የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በመተባበር ከ4 ነጥብ 34 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የኤክስሬይ መሣሪያ ድጋፍ ማድረጋቸውን የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጅ ደሳለኝ ማዕዛው ተናግረዋል።

የኤክስሬይ መሣሪያው ከፌዴራል በተላከ ባለሙያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለጹት አቶ ደሳለኝ የወረዳው ማኅበረሰብም ሕክምናውን በሆስፒታሉ ማግኘት እንደሚችል አብራርተዋል።

አቶ ደሳለኝ በተቋማቱ የተደረገው ድጋፍ ለሆስፒታሉ እና ለማኅበረሰቡ እጅግ አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰው ማኅበረሰቡ ይደርስበት የነበረውን እንግልት እና ያወጣው የነበረውን ከፍተኛ ወጭ ያስቀራል ብለዋል።

ድጋፍ ላደረጉት ተቋማትም በአካባቢው ማኅበረሰብ ስም ምሥጋና አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጥራት መንደር” ኢትዮጵያ
Next articleሰልጣኞች በተመረቁበት የሙያ መስክ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።