
ከበርካታ ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የተጀመረውን ሀገር አቀፍ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፣ “የጥራት መንደር” ኢትዮጵያ ዛሬ ልትመረቅ ነው።
የጥራት መንደር ቁልፍ ተቋማትን ያቀፈ ነው። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ናቸው።
ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት (NQI) የሀገሪቱን ደረጃዎች ልማት፣ የሥነ ልክ፣ የዕውቅና አሰጣጥ፣ የተስማሚነት ግምገማ፣ የገበያ ክትትል እና የጥራት ማስተዋወቅን በማጠናከር፣ ለንግድ ድርጅቶች የሚሰጠውን የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ለማሳደግ ያለመ ነው።
በዘመናዊ መሣሪያዎች የተደገፈው እና የተሻሻለ ዐቅም ያለው ‘የጥራት መንደር’ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር በተሻለ ሁኔታ እንድትሣለጥ፣ የቴክኒክ መሰናክሎችን እንድትቀንስ እና በዓለም አቀፍ ንግድ ያላትን ተሳትፎ እንድታሻሽል አጋዥ ይሆናል።
መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ነው።