
ወልድያ:ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሰሜን ወሎ ዞን የማጠቃለያ መርሐ ግብር የፓናል ውይይት በሀራ ከተማ ተካሂዷል።
“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ የሰሜን ወሎ ዞን እና የሀራ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች እና የሀራ ከተማ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍል በተገኙበት ውይይቱ ተካሂዷል።
የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጠፋ ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደ ሰላም፣ አንድነት እና ብልጽግና የመምራት ተልዕኮውን በጽናት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየገጠሙ ያሉ ችግሮች የብልጽግና ጉዞ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ ቀላል እንዳልነበረ ነው ያስረዱት፡፡
ኀላፊው በተለይ በክልሉ ብሎም በዞኑ የሕወሓት ተደጋጋሚ ወረራ እንዲሁም በጽንፈኛው ኀይል በዞኑ ልማት ላይ እንቅፋት ኾነው መቆየታቸውን ነው የገለጹት።
ዘረፋ እና እገታ ግብሩ የኾነው ጽንፈኛ ኀይል በክልሉ የውክልና ጦርነት እያካሄደ በመኾኑ ሕዝቡ ሰላሙን ካጣ ውሎ አድሯል ነው ያሉት፡፡
የመንግሥት ትንሹ ተልዕኮ የሕዝቦችን ደኅንነት መጠበቅ በመኾኑ ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ሕዝቡም ለሕግ ማስከር እርምጃው እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥዳዳሪ አራጌ ይመር በልጽግና ፓርቲ በ5ኛ ዓመት ጉዞው አንደ ሀገር የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሥራ፤ እንደ ክልል የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የዓባይ ድልድይ ግንባታ፣ የፋሲል ቤተመንግሥት እድሳት፤ እንደ ዞን ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት እና መሰል ትልልቅ ተጨባጭ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል።
ዞኑ እያካሄደ ባለው የራስ አቅም ልማትን ለማሳለጥ የሕዝቡ ድጋፍ ጉልህ መኾኑንም ገልጸዋል። በየደረጃው ልማት ቢኖርም የጸጥታ ጉድለቶች የልማት ሥራው ላይ እንቅፋት ኾነዋል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ በልማት ድጋፍ ያሳየውን ቁርጠኛ ተጋድሎ በሰላም እና ጸጥታ በመድገም የዞኑን ልማት የማረጋገጥ ኀላፊነት አለበትም ብለዋል።
የሀራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ሰይድ ብልጽግና ዕውን ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ በሀራ ከተማ አሥተዳደር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ኘሮጀክቶች ተሠርተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
የሀራ ከተማ ሕዝብ ለሰላም እና ለልማት ያለው ፍላጎት ከንቁ ተሳትፎው ጋር ተዳምሮ ለከተማዋ ዕድገት ሚናው ጉልህ ነበር ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!