
አዲስ አበባ:ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የማጠቃለያ መርሐ ግብሩን በዓድዋ ሙዚየም እያከናወነ ነው።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም ፋራህ በምስረታ መድረኩ ላይ ብልጽግና ፓርቲ የተመሠረተው የሃብት ብክነት ለመቆጣጠር፣ የሕዝብ ብሶትን እና ጥያቄዎችን መመለስን መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል።
ማንኛውም ፓርቲ የሕዝቡን ሰሜት መግዛት የሚችለው ካልተገባ ስሜት እና ጽንፍ ወጥቶ በተገባ ሥነ ምግባር እና በሃሳብ ልዕልና ላይ ሲመሠረት መኾኑንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።
የሕዝባችንን ችግር መፍታት የምንችለው እና ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስከበር የምንችለው በሃሳብ ልዕልና ላይ መመሥረት ሲቻል እንደኾነ አብራርተዋል።
ኅብረ ብሔራዊነትን እና አንድነትን ሚዛናዊነታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ፓርቲው ስለማድረጉ እና ወደፊትም የሚሄድበት መኾኑን አብራርተዋል።
የማኅበረሰባዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው በሃሳብ ልዕልና ላይ ተመሥርቶ ሲቆም ነው ብለዋል።
ፓርቲው በህልም ጉልበት ተመሥርቶ ለሀገሪቱ ተጨባጭ መፍትሄ አምጥቷል ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ለአባላቱ እና መሪዎች አብራርተውላቸዋል።
አንደ ፓርቲ አስተሳሳሪ የኾነ ማኅበረሰባዊ የጋራ ትርክት ማሳደግ፤ ዕውነተኛ የኅብረ ብሔራዊ ትርክት መገንባት መቻል፤ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና የተሻለ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ መቻል ፓርቲው በቅርቡ ያሳካቸው እንደኾኑም ጠቅሰዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በሀገራዊ ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ በመናፈሻ እና ቱሪዝም ልማት ግንባታ፣ በአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም በኮሪደር ልማት ተግባራዊ ማሳያ የኾኑ እና ተጨባጭ የሀገራዊ ልማት ማሳያ ኾነው ለፖርቲው ጥንካሬ ስለመኾናቸው አንስተዋል።
ያለፉትን ዓመታት ስኬት ለማስቀጠል መሪዎች እና አባላቱ ውስጠ ፓርቲ ጥንካሬን ለማሳደግ የሕዝብ ተሳትፎን በማሳደግ አንዲሁም በመልካም አሥተዳደር የበኩላቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ አካታች ኢኮኖሚውን ለመገንባት እና ማኅራዊ ፍትሕን ለማስፈን ፓርቲው ለሚያከናውነው ተግባር ሁሉም ኅብረተሰብ ድጋፍ እንዲያያደርግ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!