
ባሕር ዳር:ኅዳር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገ ወጥ ንግድ እና ነጋዴዎች የኑሮ ውድነቱን እያባባሱት እንደኾነ የከተማዋ ነዋሪዎች ያነሳሉ። የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ሕገ ወጥ ንግድ እና ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ብሏል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከሰሞኑ አካሂዷል። ጉባዔው በስፋት ከመከረበት እና ከተወያየበት ጉዳይ አንዱ የኑሮ ውድነት ተጠቃሽ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
ወይዘሮ በለጡ ታፈረ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ አንድ ኪሎ ግራም ስኳር ከ95 ብር ወደ 135 ብር፣ 100 ኪሎ ግራም ጤፍ ከ11 ሺህ ብር 16 ሺህ ብር የደረሰው ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ኾን ብለው በመከዘን እና ዋጋ በመጨመራቸው ነው ይላሉ።
በየአካባቢው መንገድ እየዘጉ የሚሸጡ ነጋዴዎች በሸቀጣ ሸቀጥ ላይ እንደ ፈለጉ ዋጋ እየጨመሩ ሲሸጡ የሚቆጣጠራቸው እና ለሕግ የሚያቀርባቸው አካል የለም ነው ያሉት። እነዚህ ነጋዴዎች ይባስ ብለውም ምርት በመከዘን ገበያውን ያስርቡታል ነው ያሉት። ምርት እና አቅርቦት እያለ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሚፈጽሙት ደባ ሕዝብን ለኑሮ ውድነት እያጋለጡት ይገኛል ብለዋል።
ሌላው አቶ መዝገቡ ቢኒያም የተባሉ ሸማች በከተማዋ የተስተዋለው የኑሮ ውድነት መንስዔው መንግሥት ከነጋዴዎች ጋር ተወያይቶ የማሳመን ሥራ ባለመስራቱ እንጅ የምርት እጥረት አጋጥሞ አይደለም ባይ ናቸው።
በቅርቡ በኪዳነ ምህረት፣ አቡነ ሐራ፣ ቀበሌ 13፣ እና ቀበሌ 04 እንዲሁም ዓባይ ማዶ ያሉትን ገበያዎች ተዘዋውሬ አይቻቸዋለሁ የሚሉት አቶ መዝገቡ የኢንዱስትሪም ኾነ የግብርና ምርት የአቅርቦት እጥረት የለባቸውም። ነጋዴዎች በነጻ ገበያ ስም ራሳቸው በሚያወጡት የዋጋ ተመን መሸጣቸው ነው ችግሩ ብለዋል።
ከማኀበራት ሱቆች አንድ ኩንታል ጤፍ በ13 ሺህ ብር ሲሸጥ ነጋዴዎች ላይ ግን ከ16 ሺህ ብር በላይ ነው። በመኾኑም ከተማ አሥተዳደሩ የኀብረት ሥራ ዩኒዬኖችን እና ማኀበራትን ሊያንቀሳቅሳቸው ይገባዋል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለከተማዋ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እንዳሉት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ወድነት ለማረጋጋት ከሕጋዊ ነጋዴዎች ጋር ተወያይተናል ብለዋል።
ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ድርጊቱ የሚፈጸምባቸውን 17 ቦታዎች በጥናት በመለየት እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።
ገበያውን ለማረጋጋትም ዩኒዬኖች እና የኀብረት ሥራ ማኀበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ጎሹ 60 ሚሊዮን ብር ድጎማ በመመደብ ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት ። የኅብረት ሥራ ማኀበራትም ባላቸው ካፒታል በአካባቢያቸው ከሚገኙ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን እየገዙ ለኀብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው። ለአብነት የፈለገ ዓባይ ዩኒዬን ጤፍ፣ መኮረኒ፣ ፓስታ፣ ፊኖ ዱቄት እና የምግብ ዘይት ለኀብረተሰቡ አከፋፍሏል፤ እያከፋፈለም ነው። በዚህ መልኩም ገበያውን ለማረጋጋት እየተሠራ መኾኑን አቶ ጎሹ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እና ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!