
አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአርሲ ዞን በ2016 /2017 የመኸር የእርሻ ወቅት ከ872 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን አቅዶ 930 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገና መሐመድ ተናግረዋል።
በተለይም ለውጭ ምንዛሬ ዕድገት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የስንዴ ፣ የቢራ ገብስ እና ባቄላ በስፋት እየለሙ ነው ብለዋል።
451 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ፣ 177 ሺህ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ እና 16 ሺህ የሚኾነው ደግሞ በምግብ ገብስ መልማቱን ነው የገለጹት።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከሚለማው 930 ሺህ ሄክታር መሬት ከ29 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል።
የግብርና ኢንዱስትሪውን ለማዘመን እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም አልሚዎች በሜካናይዜሽን እና በኩታ ገጠም እንዲያለሙ መደረጉንም ተናግረዋል።
ከለማው ውስጥ ከ700 ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም መልማቱንም አቶ ገና ጠቁመዋል።
በዞኑ ከ400 በላይ ትራክተሮች፣ ከ177 በላይ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች እና የጸረ ተባይ መድሐኒት መርጫ መሳሪያዎች ሥራ ላይ ናቸው።
በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ለማሳደግ አልሚዎች በኩታ ገጠም እንዲያለሙ ከማድረግ ባሻገር የአፈር ማዳበሪያን፣ የምርጥ ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ እንዲቀርቡ መደረጉንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!