ራስን ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል የአካባቢያቸውን ንጽህና እንደሚጠብቁ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

27

ደባርቅ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ “የአርብ የጽዳት ብርቱ እጆች” በሚል መሪ መልዕክት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። የጽዳት ዘመቻው የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። በጽዳት ዘመቻው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል።

በጽዳት ዘመቻው ወቅት ሃሳባቸውን ለአሚኮ ያጋሩት የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ፍቅሩ ታደሰ “ራሳችንን ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ አስፈላጊ በመኾኑ በጽዳት ዘመቻው ተሳትፈናል” ብለዋል። የቀበሌ 01 ነዋሪ ወይዘሮ አቡኔ ኀይሉ፣ የአካባቢን ጽዳት መጠበቅ ጥቅሙ የጋራ በመኾኑ ሁሉም በኅብረት ተሳትፏል ነው ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ማኅበረሰቡ በጋራ በጽዳት ዘመቻው መሳተፋቸውን የገለጹት የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ተወካይ ከንቲባ ሙላት እሸቴ ናቸው፡፡ የጽዳት ዘመቻው የአካባቢን ንጽህና ከማስጠበቅ አኳያ ፋይዳው የጎላ በመኾኑ የጽዳት ሥራው በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ሊግ ኀላፊ ሳምራዊት አዛናው “እንደ ፓርቲ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሴቶችን በልማት ሥራዎች ተሳታፊ ለማድረግ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ዛሬ የተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ሥራ ማሳያ እንደኾነም አስገንዝበዋል። ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ እና የከተማ አሥተዳደሩ የጽዳት እና ውበት ግብረኀይል ሠብሣቢ ሳድያ ከማል የአካባቢን ጽዳት በመጠበቅ እና በሽታን የመከላከል ሥራ በመሥራት ከተጨማሪ የሕክምና ወጭ መዳን ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ሠብሣቢዋ “ኅብረተሰቡ ሰላሙን በማጽናት በሌሎች የልማት ሥራዎችም ተሳታፊ ሊኾን ይገባል” ብለዋል።

የጽዳት ዘመቻው በተጠናከረ መልኩ በየሳምንቱ ሮብ እና አርብ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሚሠራም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተደረገልን አቀባበል የቤታችን ያህል እንዲሰማን ያደረገ ነው” አዲስ ገቢ ተማሪዎች
Next articleበአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሕዝብ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመለየት ለመፍታት እየተሠራ ነው።