የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሚያስችል ተገለጸ።

37

አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተግባራዊ የኾነው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በብዛት ለማምረት የሚያስችል መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ አመራሮች እና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የመኽር የእርሻ ሰብል ልማት እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለምግብ ፍጆታ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች የሚውሉ የግብርና ምርቶችን በከፍተኛ ወጭ ከውጭ ሀገር ስታስገባ እንደ ነበር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታው ከበደ ዴሲሳ አስታውሰዋል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱ ምርትን በብዛት እና በጥራት በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጻ እየተገበረች ነው።

በተለይም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት እና የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ በብዛት እና በጥራት በማምረት ራስን ከመቻል አልፎ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ሀገሪቱ በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት በምግብ ራስን መቻል እና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ገቢን ለማሳደግ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል ሚኒስትር ድኤታው።

በተለይም በቢራ ፋብሪካዎች የሚያጋጥመውን የቢራ ገብስ የግብዓት እጥረት ለመፍታት ምርቱ በሀገር ውስጥ በስፋት እየለማ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ድኤታው ችግሩን ለመፍታት አሁን ላይ በአርሶ አደሮች ማሳ የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ ነው ብለዋል። ምርቱ በሰፊው በማምረት ለፋብሪካዎች በብዛት ለማቅረብ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።

መንግሥት የግብርና ዘርፉን ለማበረታታት፣ ለአልሚዎች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሠራ ስለመኾኑም ሚኒስትር ድኤታው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- ቴወድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ከተማ አስተዳደር የተመረጡ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሠጡ ፈቃድ ሰጠ።
Next article“የተደረገልን አቀባበል የቤታችን ያህል እንዲሰማን ያደረገ ነው” አዲስ ገቢ ተማሪዎች