
ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለሰው ልጆች አዛኝ፤ ያላቸውን አካፍለው የሚኖሩ ደግ እና ሩህሩህ ሰው እንደኾኑ ይነገርላቸዋል እማሆይ ሁላገርሽ ብርሃኑ፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ እማሆይ ሁላገርሽ ብርሃኑ ከ18 ዓመት በፊት ጀምሮ ገበያ በመዋል የጉሊት ንግድ በመሥራት ቤት ተከራይተው ልጆቻቸውን ያሳድጉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ከ18 ዓመት በኋላ በደረሰባቸው ህመም ምክንያት ማየት እንደተቸገሩ እና ሠርተው መግባት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ልጆቻቸው ጎዳና እንደወጡ እና የሚከፍሉት የቤት ኪራይ ባለመኖሩ በየሰው ቤት እየተጠጉ በችግር ውስጥ ዓመታትን ማሳለፋቸውንም ነው ለአሚኮ የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ሠርቶ በሰጠው ቤት ተጠቃሚ መኾን ችለዋል፡፡ እማሆይ በዚህም እጅግ ደስተኛ እንደኾኑ ነው የሚናገሩት፡፡ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ መኳንንት ሙሃባው አካል ጉዳተኛ በመኾናቸው በዌልቸር ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ከዚህ በፊት ቤት ባለመኖራቸው ባለባቸው የአካል ጉዳት ምክንያት እንደፈለጉ ለመውጣት እና ለመግባት ምቹ የኾነ የቤት ኪራይ ማግኘት ፈትኗቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አሁን ክፍለ ከተማው ባመቻቸው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ የዕድሉ ተጠቃሚ መኾን ችለዋል፡፡ በዚህም ደስተኛ ናቸው፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ክፍለ ከተማ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ያስገነባቸውን 42 የመኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማ የከተማዋ ነዋሪዎች አስረክቧል።
በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የከተማ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና ርዕዮተ ዓለም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጊዜው ታከለ “በጎነት ለራስ ነው” በሚል በክረምት በጎ አድራጎት ተግባራት የተሠሩ ቤቶችን የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ 5ኛ ዓመትን ታሳቢ በማድረግ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ለማስተላለፍ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው መርሐ ግብሩ መንግሥት በመደበኛነት የማይፈታውን ችግር ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ችግሮችን የሚቀርፍበት ሥራ ነው ብለዋል፡፡ በከተማዋ ከ400 በላይ ቤቶችን ሠርቶ ለማስረከብ በታቀደው መሠረት ከ100 በላይ አዲስ ቤት በመገንባት እና ከ400 በላይ ጥገናዎችን በማድረግ በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ማኅበረሰቡን የማሳተፍ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ ውጤት የሚመጣው፣ ድልም የሚሳካው መላው ማኅበረሰብ የኔ ድጋፍ ምን ታደርጋለች ሳይል ያለውን ሲያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ኀላፊዋ በክልሉ ያሉ አቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንዳቅሙ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡
ሥራ መሥራት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ኀላፊዋ ክልሉ ከገባበት ቀውስ ለማውጣት ሁልጊዜም ከሚሠሩ ሥራዎች ባሻገር ለስላም ዘብ መቆም ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ቤቶቹ በዕጣ ለነዋሪዎቹ የተላለፉ ሲኾን በገንዘብ እና በአይነት እገዛ ላደረጉ ተቋማት እና ግለሰቦችም የምሥጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
