”የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የበለጠ መሥራት ይጠይቀናል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

44

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የ2017 በጀት ዓመት የአራት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ከሠራተኞቹ ጋር ገምግሟል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የአራት ወር እቅድ አፈጻጸማችን ስንገመግም ጥንካሬያችን ለማስቀጠል፣ ጉድለቶቻችን ለማረም እና ለቀጣይ ዕቅዳችን መሳካት አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለማወቅ ያግዘናል ብለዋል።

ባለፉት አራት ወራት በተሠሩ ሥራዎች ሰፊ ርብርብ ተደርጓል፤ የክልሉን ምክር ቤት ጉባኤ በማካሄድ፣ እቅዳችንም በተዋረድ ተግብረን ፈጻሚውንም ያዘጋጀንበት እና ገለጻ የሰጠንበት ነበር ብለዋል። በዚህም የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች አስተዋጽኦ መልካም እንደነበር ገልጸዋል።

በክልሉ ከነበረው የሰላም ችግር አኳያ ሲታይ መልካም የሚባሉ የአፈጻጸም ጅምሮች ቢኖሩም ኅብረተሰቡ ከሚፈልገው አኳያ ሲታይ ግን “በቀጣይ የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል” ነው ያሉት። በተለይ ምክር ቤቶችን በመደገፍ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው በማጠናከር በኩል መሥራት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመን በተናጠል እና በጋራ በመሥራት የድርሻችን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል። በቀረበው የጽሕፈት ቤቱ የአራት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የክልሉን ምክር ቤት ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር እና የሕዝብ ውክልናን የመወጣት ኀላፊነቶቹን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር እና በማገዝ ተግባር ተከናውኗል።

የሥራ እቅዶች ተዘጋጅተው ለየደረጃው ምክር ቤቶች የእቅድ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸምም ተገምግሟል ተብሏል። ለተዋረድ ምክር ቤቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣ የአፈ ጉባኤዎች እና የወረዳ ሴት ተመራጮች ፎረም ማካሄድ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሠራታቸውም ተመላክቷል።

የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች በአመለካከት፣ በአደረጃጀት፣ በአሠራር እና በግብዓት አቅርቦት አሻሽሎ ለምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የተሠራው ሥራም ተዘርዝሯል። የታዩ እጥረቶችም ተጠቁመዋል። ምክር ቤቶች ጉባኤያቸውን እንዲያካሂዱ ድጋፍ በማድረግ እና የክልሉን ምክር ቤት ጉባኤ የማመቻቸት ሥራ መሠራቱም በሪፖርቱ ተገልጿል።

በአገልግሎት አሠጣጥ የደንበኞች እርካታን ለማሳደግ፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለን ግንኙነት በማጠናከር አብሮነትን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ፈጣን እና ጥራት ያለው ሥራ መሥራት እና መረጃዎችን ለሕዝብ የማድረስ ሥራ መተግበር ዋና ዋና የተከወኑ ሥራዎች ነበሩ። ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት መሠራቱም ተጠቅሷል።

የምክር ቤት ጽሕፈት ቤቱ የእቅድ እና በጀት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር በሪሁን ፉፋ የክልሉን ምክር ቤት ተልዕኮዎች ለመፈጸም ጽሕፈት ቤቱ አቅዶ እያገዘ መኾኑን ገልጸዋል።በርካታ የወረዳ ምክር ቤቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ጉባኤያቸውን አለማካሄዳቸው በእጥረት መታየቱን ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) በመራጭ ተመራጭ ውይይት እንዲሁም የተዋረድ ምክር ቤቶችን በመደገፍ አቅም የማሳደግ ሥራውን በመሥራት በኩል ጽሕፈት ቤቱ ማገዙን ነው የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመምህራን ትውልድ የመቅረጽ ሙያቸውን በፍቅር ይዘው በመሥራት ለነገዋ ኢትዮጵያ መሠረት የሚኾን ማፍራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።
Next articleየእማሆይን ችግር የቀረፈው በጎ ሥራ!