መምህራን ትውልድ የመቅረጽ ሙያቸውን በፍቅር ይዘው በመሥራት ለነገዋ ኢትዮጵያ መሠረት የሚኾን ማፍራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

63

ሰቆጣ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ “የመልካም ዜጋ መነሻው የአዕምሮ ልማት ነው” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው። በውይይቱ የሥነ ምግባር መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና የትምሕርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ እንደሀገር የገባንበት የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያቱ አባቶቻችን ያቆዩትን የመከባበር፣ የመደጋገፍ እና የመፈቃቀር እሴቶች በመሸርሸራቸው ነው ብለዋል።

ከዚህ ለመውጣት የመምህራን ቁርጠኛ ኾነው ልጆችን በሥነ ምግባር እና በዕውቀት መቅረጽ አለባቸው ነው ያሉት ከንቲባው። የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች እና መምህራን በልጆች አዕምሮ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የኾኑት መምህርት ማሬ ሽፈራው የዘመኑን ቴክኖሎጂ ባልተገባ ሁኔታ መረዳት እና መጠቀም ለተማሪዎች የሥነ ምግባር ውድቀት አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል። የወላጆች ቁጥጥር ማነስም ችግሩን አባብሶታል ነው ያሉት። ከዚህ ችግር ለመውጣት የሥነ ምግባር እና የግብረ ገብ ትምህርቶችን በቃል ሳይኾን በተግባር ልናስተምር ይገባል ብለዋል መምህርቷ።

ሌላው አስተያየት ሰጪ መምህር ዘውዱ ጌታሁን ሀገር በቀል ያልሆነ የትምህርት ሥርዓት መኖሩ በተማሪዎች ላይ የሥነ ምግባር ጉድለት አስከትሏል፤ አንዳንዶችንም የሱስ ተጋላጭ አድርጓቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ የተጀመሩ የግብረ ገብ፣ የሥነ ምግባር እና የሥነ ዜጋ ትምህርቶች ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ይዘው መምጣታቸው ለተማሪዎች ስነ ምግባር መሻሻል እንደሚያግዙም መምህሩ ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የወለህ ነቅዓ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን መምህር መዝገበ ቃል ገብረ ሕይወት “ዛሬ የትውልዱን ሥነ ምግባር በማነጽ ነገ የተረጋጋች እና ሰላሟ የሰፈነች ሀገር መገንባት እንችላለን” ሲሉ ገልጸዋል። “እንደ ሀገር እየተከፈለ ያለው ዋጋ ትላንት ያልተሠራ ሥራ እንደነበር ያመላክታል” ያሉት መምህሩ ነገም ከዚህ የከፋች ሀገር እንዳትኖረን ዛሬ ላይ መልካም እሴቶቻችንን ለልጆቻችን ማሳየት እና ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት።

“ወደን ከማንሠራው ሥራ የሚጠበቅ ውጤት አይኖርም” የሚሉት መዝገበ ቃል እያንዳንዳችን የምንሠራውን ሥራ ወደን እና ፈቅደን ከሠራን ውጤታችን ያማረ ነው ሲሉ ገልጸውታል። መምህራን ትውልድ የመቅረጽ ሙያቸውን በፍቅር ይዘው በመሥራት ለነገዋ ኢትዮጵያ መሠረት የሚኾኑ ምግባረ ሰናይ ልጆችን ማፍራት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ትምሕርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታምሩ ካሳሁን ሁሉም በጋራ በመቆም ለሀገር የሚበጅ ትውልድ መቅረጽ ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም መምህራን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ያሳሰቡት ኀላፊው በቀጣይም ከተማሪዎች፣ ለተማሪ ወላጆች እና ለትምህርት ባለድርሻ አካላት መሰል የሥነ ምግባር ግንባታን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመመከት እያደረገች ያለው ጥረት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው እንደኾነ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
Next article”የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የበለጠ መሥራት ይጠይቀናል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ