
አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለማቀፍ አውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም ተካሂዷል። የአየር ንብረት ለውጥ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዓለምን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት የሰው ልጆች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የግድ ብሏቸዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ተግባራዊ ሥራዎችን ከጀመረች ሰነባብታለች። ከእነዚህ ሥራዎቿ መካከልም ያላትን የተከማቸ ታዳሽ ኀይል በመጠቀም የነዳጅ ጥገኝነትን መቀነስ፤ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን መጠቀም እና ብሎም የሚለቀቀውን የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀትን የመቀነስ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በሁዋጂየን የኢንደስትሪ መንደር የተካሄደው ኢትዮ ግሪን 2024 ዓለማቀፍ አውደ ርዕይ እና ስፖዚየም የዚሁ ማሳያ እንደኾነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የነዳጅ ጥገኝነትን እና የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እያደረገችው ያለው ተግባራዊ ጥረት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመመከት በኩል ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው እንደኾነ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ.ር) መድረኩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለውን ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን እምቅ የታዳሽ ኀይል ሃብት ባለቤትነት የገለጹት ሚኒስትሩ ይሄን መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም የግሪን ተሽከርካሪ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ተግባሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ከፍተኛ የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች የተገኙበት፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፤ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትን የሚቀንሱ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ለዕይታ የቀረቡበት አውደ ርዕዩ ከኅዳር 13 /2017 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ይቆያል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
