የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመርቃል።

90

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ (ፒ ኤች ዲ) መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ አመራሮች ኅዳር 14/2017 ዓ.ም ይመረቃሉ።

በምክትል ቢሮ ኀላፊ ደረጃ የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጋሻው ገብሬ ኢንስቲትዩቱ ሲቋቋም ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሪዎችን አብቅቶ ለማውጣት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

መሪዎቹ በዕውቀት እና በክህሎት የዳበሩ፣ በአወንታዊ አስተሳሰብም የተጠናከሩ እንዲኾኑ በትኩረት የሚሠራ ኢንስቲትዩት ስለመኾኑም አንስተዋል።

ለዚህም ኢንስቲትዩቱ አጫጭር ሥልጠናዎችን ይሰጣል፣ መደበኛ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቶችን በብቁ መምህራን ያስተምራል፤ ምርምሮችንም ይሠራል ነው ያሉት ኀላፊው።

ኢንስቲትዩቱ ከትምህርት ሚኒስቴር በተሠጠው ፈቃድ መሠረት ከሁለተኛ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒ ኤች ዲ) ድረስ ትምህርት እየሰጠ ነው።

በሁለት የትምህርት መስኮች ማለትም በፓለቲካል ኢኮኖሚ እና በመንግሥት አሥተዳደር የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያስተማረም ነው።

በአራት የትምህርት መስኮች ማለትም በፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በፐብሊክ ፖሊሲ እና አመራር እንዲሁም በፖለቲካል ኢኮኖሚ ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ትምህርት እየሰጠ ነው።

ኢንስቲትዩቱ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያስመርቃል።

የምርቃት መርሐ ግብሩ ኅዳር 14/2017 ዓ.ም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት ይካሄዳል።

በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር 221 መሪዎች የሚመረቁ ሲኾን ትምህርቱን በብቃት በማጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ጽሑፎችን ያሳተመ አንድ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪም ይመረቃል።

ከተመራቂ መሪዎች ውስጥ 58ቱ ሴቶች ስለመኾናቸውም አቶ ጋሻው ገልጸዋል። ይህም ክልሉ ለሴት መሪዎች የሰጠውን ትኩረት እና አቅማቸውን ለማላቅ የሚሠራውን ሥራ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ነጻነትን እና የአፍሪካን ሰላም ለመጠበቅ ያደረገችውን አስተዋጽኦ የሚያስተዋውቅ ኮንፈረንስ እንደሚያካሂድ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመመከት እያደረገች ያለው ጥረት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው እንደኾነ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።