ሰብዓዊነትን በማስቀደም ደም መለገስ እንደሚገባ የደብረ ማርቆስ ከተማ ደም ባንክ አገልግሎት አሳሰበ።

37

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማንኛውም ሰው ከ18 ዓመት እስከ 65 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እና ክብደታቸው ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የኾኑ ጤናማ ሰዎች በየሦት ወሩ በቋሚነት ደም መለገስ እንደሚችሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ደም እንደሚለግስ የነገረን የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይልቃል አንዳርጌ ደም መለገስ ከሚሰጠው የህሊና እርካታ በላይ ለወገን ደራሽነታችን ማሳያ በጎ ተግባር ነው ይላል፡፡

ደም መለገስ የሚያጎድለው ነገር የለም የሚለው ወጣት ይልቃል እናቶች እና ሌሎች ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ሕይዎት ለመታደግ ሁሉም በፈቃደኝነት ደም ሊለግስ እንደሚገባም ነው የነገረን፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ ደም ባንክ አገልግሎት ኀላፊ ከፋለ ገበየሁ በበጀት ዓመቱ ከ10 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ከበጎ ፈቃደኞች ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው የገለጹት።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜው ድረስ 70 በመቶ የሚኾነውን ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ይህም ካለው አሁናዊ የደም ፍላጎት አንጻር በቂ ባለመኾኑ ደም የመሠብሠብ አቅምን ከፍ ለማድረግ የሁሉንም ድጋፍ እና ፈቃደኝነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በወሊድ ጊዜ ደግም ለሚያስፈልጋቸው እናቶች እና ሕጻናት እንዲሁም ለሌሎች ወገኖች ሕይዎት ለመታደግ ደም መለገስ ይገባል ሲሉ ኀላፊው አስገንዝበዋል፡፡

በየትኛውም ጊዜ ደም የሚያስፈልግ በመኾኑ ሰብዓዊነትን በማስቀደም ደም መለገስ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዋናው የደም ባንክ አገልግሎት እና በከተማዋ በተዘጋጁ የተለያዩ ማዕከላት በመገኘት ኅብረተሰቡ ደም እንዲለግስም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚሊሺያ እና ሰላም አስከባሪ አባላት የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ እየሠሩ ነው።
Next articleየወልድያ ከተማ አሥተዳደር የኮሌራ መከላከያ ክትባት መስጠት ጀመረ።