የሚሊሺያ እና ሰላም አስከባሪ አባላት የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ እየሠሩ ነው።

52

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል የሕይወት እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የሚሊሻ አባላት እና የሰላም አሥከባሪ አባላት የካሳ ክፍያ መፈጸሙን የአማራ ክልል ሚሊሺያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በ2013 ዓ.ም በነበረው ከሰሜኑ ወረራ ጋር በተያያዘ በክልሉ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ክልሉ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የሚሊሺያ፣ የሰላም አስከባሪዎች፣ የግል እና የመንግሥት ታጣቂዎች መሳተፋቸውን የአማራ ክልል ሚሊሺያ ጽሕፈት ቤት የሰው ሃብት አሥተዳደር ዳይሬክተር ደምስ ስለሽ ገልጸዋል።

ወረራውን ለመከላከል በተካሄደው ጦርነት የሕይወት እና የአካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረት ወድሟል። አንድ ሰው በስምሪት ላይ እያለ የሕይወት መስዋዕትነት ከከፈለ 100 ሺህ፣ ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰበት 80 ሺህ እና ቀላል ጉዳት ከደረሰበት ደግሞ 60 ሺህ ብር ካሳ እና ድጎማ እንደሚከፍል የክልሉ መንግሥት በመመሪያ እና በደንብ ማስቀመጡን ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት በሕወሓት ወረራ ወቅት ሕግ ለማስከበር ጉዳት ለደረሰባቸው ሰላም አስከባሪዎች፣ የሚሊሺያ አባላት፣ የግል እና የመንግሥት ታጣቂዎች እንዲኹም ሌሎች በትግሉ ለተጎዱ እና ለተጎጅ ቤተሰቦች የክልሉ መንግሥት ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን ገልጸዋል።

አሁን ላይም ክልሉ ካጋጠው የውስጥ ችግር ጋር ተያይዞ የክልሉ የሚሊሺያ እና ሰላም አስከባሪ አባላት ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ሰላም የማስከበር ሥራ እያከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።

በስምሪት ሂደቱ ላይ ጉዳት የሚያጋጥማቸውን የሚሊሺያ መዋቅር አባላት አስፈላጊውን ካሳ እና ድጎማ ለመክፈል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የሚሊሺያ እና ሰላም አስከባሪ አባላት ማኅበረሰቡን በማስተባበር የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ እየሠሩ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ የሰላሙን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ አጋዥ እንዲኾንም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር 42 የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች አስረከበ።
Next articleሰብዓዊነትን በማስቀደም ደም መለገስ እንደሚገባ የደብረ ማርቆስ ከተማ ደም ባንክ አገልግሎት አሳሰበ።