
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ወንዳጣ ቀበሌ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሕዝብ የሰላም ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የሀገር መከላከያ እና የሰሜን ጎጃም ዞን የጸጥታ አባላት ተገኝተዋል።
በውይይቱ የተገኙት የምሥራቅ ዕዝ የገርባሳ ማሠልጠኛ ማዕከል የሥልጠና ክፍል ኀላፊ ሌተናል ኮሎኔል ደሳለው ኪሮስ እንዳሉት “ጽንፈኛው ቡድን” በፈጠረው የሰላም ችግር በመንግሥት ተቋማት ላይ ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሟል፤ የልማት ሥራዎችም ተቋርጠዋል።
ይሁን እንጅ ማኅበረሰቡ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የደረሰውን ጉዳት በመረዳቱ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመኾን ሰላሙን ለማስጠበቅ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
እስከ አሁን በተሠራው ሥራ የፈረሱ ተቋማትን በማደራጀት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
ወደ ሥራ ያልገቡ ተቋማት ወደ ተሟላ ሥራ እንዲገቡ የማኅበረሰቡ ጥያቄ መኾኑን ያነሱት ሌተናል ኮሎኔሉ የሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥትም ማኅበረሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሊሰጥ ይገባልም ነው ያሉት።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ቡድኖችንም የጸጥታ መዋቅሩ ተቀብሎ የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም የሰላም ጥሪውን የሚቀበሉ ቡድኖችን ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
መሳሪያን አማራጭ አድርጎ ወደ ጫካ የወጣ ማንኛውም አካል ለሀገር የሚጠቅም አለመኾኑን ተገንዝቦ በሰላም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
