የሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወጣቶችን የሙያ ባለቤት እያደረገ ነው።

18

ሰቆጣ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት መኳንንት ልብሱ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ነው። ከአራት ዓመታት በፊት በግንባት ትምሕርት ዘርፍ ከሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተመርቋል።

ወጣቱ እንደ አብዛኛዎቹ ተመራቂዎች የመንግሥት ሥራ በመፈለግ ወርቃማ የወጣትነት ጊዜውን ማባከን አልፈለገም። አብረውት ከተመረቁ ሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በመኾን የብረታ ብረት ብየዳ ቤት በመክፈት ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው።

“የሥራ መሰረቴ ሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ነው” የሚለው ወጣት መኳንንት ለሦስት ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉም እንዳስደሰተው ተናግሯል። የከተማ አሥተዳደሩ የመሥሪያ ቦታ እንደሰጠውም ገልጿል። ኮሌጁም አስመርቆ ከመተው ይልቅ በየጊዜው የሙያ እገዛ እና የብረታብረት ሥራ እንድንሠራ ያግዘናል ነው ያለው ወጣቱ።

ወጣት መኳንንት በቀጣይም ከጓደኞቹ ጋር በመኾን የብረታ ብረት ሥራ ድርጅቱን ለማስፋፋት እንደሚሠሩ ገልጿል።

የሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ1999 ዓ.ም የተመሰረተ ሲኾን በ2012 ዓ.ም ደግሞ ወደ ፖሊ ቴክኒክነት ደረጃ ማደግ ችሏል። ከ15 ጊዜ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀው ኮሌጁ ከ5 ሺህ በላይ ሠልጣኝ ተማሪዎችን የሙያ ባለቤት ማድረጉን የኮሌጁ ዲን አቶ ሰሎሞን ወርቁ ገልጸዋል።

ከተመረቁት ውስጥ ወደ 1 ሺህ የሚኾኑትን በልዩነት እየተከታተሉ በሥራቸው ውጤታማ እንዲኾኑ ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል። በዘንድሮው ዓመትም በ15 የትምህርት መስኮች ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 ድረስ ለማሠልጠን የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለወጣቱ ቀዳሚ የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደኾኑ የሚናገሩት አቶ ሰሎሞን ኮሌጁ በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ቢደርስበትም ከመንግሥት እና አጋዥ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ በሙሉ አቅሙ ተማሪዎችን ለማሠልጠን ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ነባር ሠልጣኞችን እስከ ደረጃ አምስት ድረስ እያሠለጠነ እንደሚገኝ ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወረባቦ ወረዳ የእናቶች መለስተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ማዕከል ተመረቀ።
Next articleየጸጥታ መዋቅሩ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ቡድኖችን ተቀብሎ በማሠልጠን ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ነው፡፡