
ደሴ: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሆስፒታሎች በቅርበት በሌሉበት ወረዳ እና ከተሞች ላይ የእናቶች ቀዶ ሕክምና መስጫ ማዕከላትን እየገነባ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ገልጿል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ እስካሁን በስድስት ወረዳዎች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ላይ ማዕከሉን በመገንባት እናቶች እና ህጻናት ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ማስቻሉን እና በቀጣይ በሌሎች ወረዳዎችም እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በወረባቦ ወረዳ የቢስቲማ ከተማ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ፍስሃ ስንታየሁ የቀዶ ሕክምና ማዕከሉ መገንባት በተለይ በወሊድ ወቅት ቀዶ ጥገና ሲያስፈልጋቸው ወደ ሐይቅ እና ደሴ ሪፈር ስለሚባሉ ለሞት እና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ በቅርበት አገልግሮቱ መጀመሩ ችግሩን ይቀርፋል ብለዋል።
አግልግሎት መስጠት በጀመረ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 10 እናቶችን በቀዶ ሕክምና ማወለድ መቻሉንም ገልፀዋል።
20 ሚሊዮን ብር በማውጣትም የኬሚስትሪ የሲባሲ ማሽን እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶች ግዢ መፈጸሙንም ነው የጠቆሙት። በቀዶ ሕክምና ማዕከሉ አገልግሎት ያገኙት የቢስቲማ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ አሕመድ እና ወይዘሮ ረሕመት መሐመድ ሪፈር ተብለው ሐይቅ እና ደሴ መሄዳቸው ብቻ ሳይኾን የሚጓዙበት አምቡላንስ እያጡ ብዙ ስቃይ ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ማዕከሉ በቅርበት በመገንባቱ ከብዙ እንግልት እና ድካም እንዳዳናቸው እና ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም እናቶች የሁሉም ነገር መሠረት መኾናቸውን ገልጸው የጤናው መስክ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው አንዱ እና ዋናው የእናቶች እና ህጻናትን ሞት መቀነስ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ሙሐመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
