
በሰላም ተምሳሌቷና ጎተራዋ ሙሉ በሆነችው ደጀን ወረዳ ባየነው የጤፍ ክላስተር ልማት ተደንቀናል።
ኢትዮጵያን ወደከፍታዋ መውሰድ የምንችለው በግብርና እና ሌሎች የልማት መስኮች የጀመርናቸውን ሥራዎች በማጠናከር ነው። ለዚህም እንደ ሀገር ለክላስተር ግብርና የሰጠነው ትኩረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ይገኛል።
በአማራ ክልል ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የተመለከትነው ጤፍን በክላስተር የማልማት ሥራ የሚደንቅ ነው።
በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለግብዓት አቅርቦትና ለዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታችን ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ተዘዋውረን የተመለከትነው የሰብል ቁመና ያሳያል። በቀጣይም ለመስኖ ልማት እና ለሰላም ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን።
ማኅበረሰቡም የሰላምና የልማት አርበኝነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። የምስራቅ ጎጃም ዞን ሕዝብ በተለይም የደጀን ወረዳና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላሳዩን ድንቅ የጤፍ ልማትና ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል ከልብ እናመሠግናለን።
