
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። በከተማዋ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑት መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ድልድዮች፣ መንገዶች፣ የመዝናኛ ማዕከላት እና ሌሎች ይገኙበታል።
የተሠሩትን የልማት ሥራዎች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የጎንደርን ሙሽራነት እንደገና መመለስ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን መርቀናል ብለዋል። ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት ፕሮጀክቶች ጎንደርን በቀጣይ በልማት ተወዳዳሪ እንድትኾን የሚያደርጉ፣ የልማት ሃሳቦች የሚፈልቁባቸው እና ትውልድ የሚማርባቸው ናቸው ነው ያሉት።
ለጎንደር እድገት አስተዋጽኦ በሚያደርጉት ሥራዎች ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ልማቶቹ የጎንደርን ትንሳዔ እና ሕዳሴ የሚመልሱ ናቸው ብለዋል።
የጎንደር ሊቀ መኳሶች “ጎንደር ዛሬም አዲስ ሙሽራ ናት” ብለው እንደሚቀኙ የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሙሽራነት ውስጥ አዲስነት፣ የሃሳብ እድገት፣ ነገን አርቆና አልቆ ማየት፣ መተንበይ፣ ለነገ መሥራት አለ ነው ያሉት። በሙሽራነት ውስጥ ችግሮችን በውይይት እና በጥበብ የመፍታት ሂደት መኖሩንም አመላክተዋል።
የጎንደር ሙሽራነት ነገ ያማረ እንዲኾን የገጠሙንን ችግሮች በጥበብ እየፈታን፣ እየበዛን፣ አንድ እየኾን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ጎንደር በቀደመ የታላቅነት ታሪኳ እና እሳቤዋ እንድትኖር ማድረግ እና ተጨማሪ ታሪኮችን መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ጎንደር የኪነ ጥበብ፣ የሃይማኖት፣ የሥነ ጽሑፍ ከተማ ናት ብለዋል። “ጎንደር የኢትዮጵያን ሥልጣኔ እና ታሪክ ከፍ አድርጋ በሕያውነት የምታሳይ ከተማ ናት” ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ። እንዲህ ዓይነት ከተማ እና ሕዝብ የሥልጣኔ ማሰያና ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ሥልጣኔን ስናስብ ሃይማኖትን፣ ኪነ ሕንጻ፣ ሥነ መንግሥትን ብቻ ሳይኾን በውስጡ ያለውን መተሳሰብ ማሰብ አለብን ነው ያሉት። ጎንደር በታሪኳ ውስጥ ትኑር ስንል ለሥነ መንግሥት ያላት አመለካከት እንደ ድሮው ይሁን ማለችን ነው ብለዋል። ጎንደር በሥነ መግንሥትነት ታሪክ ታላቅ አሻራ ያላት፣ ሥነ መንግሥትን የምታስቀጥል፣ መንግሥት አቅም ባነሰው ጊዜ አቅሙን የምታበረታ መኾኗን ነው የተናገሩት።
አሁን የጎንደርን ልማት ወደ ኋላ ለሚመልሱ አካላት የጎንደርን የሥነ መንግሥት ታሪክ መርምሮ በመንገር ተው ማለት እንደሚገባም ገልጸዋል። ዛሬ ላይ የገጠሙ ችግሮችን መመርመር እንደሚገባም ተናግረዋል። ጎንደር ዛሬም እንደ ታሪኳ የታላላቆች፣ የሀገር ጠበቃ እና ዋስ የኾኑ ሊቃውንት መፍለቂያ እንጂ ሞቅ ያለው ሁሉ እየተነሳ ልማት የሚያደናቅፉባት እንዳትኾን መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ከመሪዎች ጋር በመኾን ሰላሙን እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል። ጎንደር የሰላም ደሴት ስትኾን ሁሉም አቅሞች ወደ ልማት እንደሚዞሩም ተናግረዋል። የጎንደር ትንሳዔ እና የሕዳሴ ዘመን እንዲረጋገጥ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
መሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ወደ ልማት እንዲመልሱ መደግፍ እና ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። መሪዎች ተረጋግተው እንዲሠሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደርን የሕዳሴ ዘመን ለማረጋገጥ የሕዝቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!