
ጎንደር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት ትምህርት ቤቶች፣ ድልድዮች፣ መንገዶች፣ መዝናኛ ቦታዎች እና ሌሎች ናቸው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የመሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ከተሜነት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከተሜነት ሲያድግ ደግሞ ለከተሜነት አስፈላጊ የኾኑ ሥራዎች ያስፈጋሉ ነው ያሉት። በክልሉ በከተሞች ላይ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ከተሞች መሠረተ ልማቶቻቸው የተመቻቹ መኾን አለባቸው፤ ከሚለሙ መሠረተ ልማቶች መካከል ደግሞ መንገድ እና ድልድዮች ናቸው ብለዋል። የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ምቹ የኾኑ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
“ጎንደር ሥራ ላይ መኾኗን ተመልክተናል” ያሉት ኃላፊው በከተማዋ በተቀላጠፈ ኹኔታ የኮሪደር ልማት እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል። የቤተ መንግሥቱ ጥገና እና የኮሪደር ልማቱ ቀን ብቻ ሳይኾን ሌሊትም ጭምር እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን እየደገፉ ላሉ እና በሥራው እየተሳተፉ ለሚገኙት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። የኮሪደር ልማት ለከተሞች እድገት ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት ሥራ ለቀጣይ ትውልድም ጠቃሚ መኾኑን ነው የገለጹት።
የጎንደር ነዋሪዎች ለመሠረተ ልማት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሰላማቸውን አጥብቀው እንዲጠብቁም አሳስበዋል።
ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ለመሠረተ ልማቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!