የአመለካከት እንጅ የአካል ጉዳት በሥራ ከመለወጥ እንደማያግድ የአካል ጉዳተኞች ገለጹ፡፡

99

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ለ33ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን በባሕር ዳር ከተማ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሮ ውሏል። ቀኑ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታች እና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተከበረው።

የዚህ ዓመት የአካል ጉዳተኞች ቀን በወረዳ እና በክፍለ ከተሞች ደረጃ ከኅዳር 10/2017 ዓ.ም እስከ ኅዳር 15/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ እንደሚውል ተገልጿል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ቀኑን በውይይት እና በሌሎች መርሐ ግብሮች አክብሮ ውሏል።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበረው አካል ጉዳተኛ መለሰ ጥላሁን አካል ጉዳተኝነቱ ከሥራ አግዶት እንደማያውቅ ያስረዳል፡፡ በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ተሰማርቶም መቆየቱ ለዚሁ ማሳያ እንደኾነ ገልጿል።

ሌላዋ አካል ጉዳተኛ ሕሊና ሙጨ በጋዜጠኝነት ሙያ የመጀመሪያ ድግሪዋን ይዛለች። በጊዜያዊነትም በዘርፉ እየሠራች እንደኾነ ገልጻለች። ሰው በሚገባ ካስተዋለ እና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ አካል ጉዳተኝነት ማንኛውንም ነገር ከመከወን አያግድም ትላለች። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን ዋና ሠብሣቢ ዳንኤል አበበ በባሕር ዳር ከተማ ከ5 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ገልጸዋል።

የዚህን ዓመት የአካል ጉዳተኞች ቀን ሲከበርም ትርጉም ባለው እና በችግር ውስጥ ያሉትን ወገኖች ዘላቂ ሕይዎት ሊቀይር በሚችል መልኩ መኾን እንዳለበት ተናግረዋል። በዘርፉ ከተሠማሩ ረጅ ድርጅቶች እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለአካል ጉዳተኞች የገንዘብ፤ የመሥሪያ ቦታ፤ የብድር አገልግሎት፤ እና ሌሎች ድጋፎችን ሲሰጡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። የሕይወት ክህሎት ሥልጠናም ሲሰጣቸው እንደቆየ ነው የተናገሩት።

የአመለካከት እንጅ የአካል ጉዳተኝነት ከምንም እንደማያግድ በመገንዘብ በተለያዩ ሙያዎች ላይ በመሰማራት ዘላቂ ሕይዎታቸው እንዲቀየር መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴፌሽን ፕሬዚዳንት ፍሬ ስብሐት ዘገየ የዚህ ዓመት የአካል ጉዳተኞች ቀን ከወረዳ ጀምሮ በንቅናቄ እንደሚከበር ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ ይታሰባልም ነው ያሉት። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ 98 በመቶ የሚኾኑት በክልሉ ያሉ አካል ጉዳተኞች በችግር ላይ ያሉ ናቸው ብለዋል። ይህ ሁሉንም ሊያሳስበው እንደሚገባም ጠቁመዋል። የአካል ጉዳተኛን ሕይዎት ያለወጠች ሀገር ልታድግ የማትችል በመኾኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት ሊደግፋቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የአካል ጉዳተኞች የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

የማጠቃለያ መርሐ ግብሩም ኅዳር 24/2017 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚከበር የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጎንደር የትምህርት ማዕከል የሚል የክብር ስም ያላት ናት” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ደኘው
Next article“ጎንደር ሥራ ላይ መኾኗን ተመልክተናል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)