
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተገነቡ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የቢሮ ኀላፊዎች፣ ከንቲባዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በትውልድ ሂደት ውስጥ ትምህርት እና ትውልድ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም ብለዋል። ምግብ ለአካላዊ፣ አዕምሯዊ አቅማችን እና ጤንነታችን የሚያስፈልግ እንደኾነ ሁሉ ትምህርት እና እውቀትም ለሰብዓዊ ዕድገታችን ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት መጀመር 100 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለትምህርት መጀመር በቤተክርስቲያን የአብነት እና በመስጂድ የቁራን ትምህርት ቤቶች መጀመሪያዎቹ እንደኾኑ ነው ያነሱት።
ጎንደር ጥንታዊውን መደበኛ ትምህርት በመጀመር፣ በማስፋፋት እና በማሳደግ “ጎንደር የትምህርት ማዕከል” የሚል የክብር ስም እስካሁንም ያሰጣት ኾኗል ነው ያሉት። በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ በ87 ትምህርት ቤቶች ከ93 ሺህ በላይ ተማሪዎች እየተማሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ደግሞ 28 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመለሱ ኾነዋል ነው ያሉት። ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሰላምን በዘላቂነት ማጽናት የሁላችን ኀላፊነት ነው ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች በከተማ አስተዳደሩ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በአልማ እና በተቆርቋሪ ወገኖች መሥራታቸውን ገልጸዋል
የመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን በትኩረት መሥራት የዘወትር ተግባራቸው መኾኑንም ተናግረዋል። የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!