
አዲስ አበባ፡ ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የቁልፍ መሠረተ ልማት ደኅንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት ከጥቅምት 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር በተለያዩ ሁነቶች በመላ ሀገሪቱ ሲከበር የቆየው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር በስኬት ተጠናቅቋል።
የሳይበር ደኅንነት ወር መጠናቀቅን አስመልክቶ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ኃይሉ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሳይበር ደኅንነት ወር የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ስለመሠራታቸው ነው የተናገሩት፡፡
በሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ጉዳዮች እንዲሁም በስማርት ሲቲ እና ዲጂታል መታወቂያ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን አስገንዝበዋል፡፡
የሀገሪቱን የሳይበር ምኅዳር ለማስጠበቅ ከሚረዱ ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ተሻሽሎ የጸደቀው የሀገሪቱ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ስለሚኖረው ሚና ሰፊ ምክክር እንደተደረገም ነው ያብራሩት
ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!