“ከተባበርን ሁሉን ማድረግ የሚያስችል አቅም አለን” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

40

ጎንደር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተገነቡ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የልማት ሥራዎችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። ትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች፣ ድልድዮች እና ሌሎችም የልማት ሥራዎች ተመርቀዋል። የልማት ሥራዎቹ በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነቡ ናቸው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ክልሉ በትምህርት ዘርፉ እንዳይወዳደር ፈተናዎች እየገጠሙት መኾኑን ተናግረዋል። ጠላቶች በትምህርት ዘርፉ ፈተና ቢያበዙም ቅን ልቡና ያላቸው ጀግኖች ደግሞ በመተባበር ችግሩን ለመሻገር ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ትምህርት ለመኖር መንገድን የሚያስተካከል ብቻ አይደለም ያሉት ኀላፊዋ ትምህርት የመኖር ያለ መኖር ጉዳይ ነው ብለዋል። አባቶች ሳይማሩ ከቅኝ ግዛት ነጻ አድርገዋት ያቆዩዋትን ኢትዮጵያን በሠለጠነው ዘመን በትንሽ ዕውቀት አሳልፈን እንዳንሰጥ በትምህርት የሠለጠነ ትውልድ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት። ይህ ካልኾነ በስተቀር በዘመናዊ ቅኝ ግዛት ውስጥ እንደምንገባ መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ልጆቻችን አዋቂ እና ተመራማሪ እንዲኾኑ፣ በምክንያት የሚደግፉ እና በምክንያት የሚቃወሙ፣ የራሳቸውን መንገድ የሚወስኑ ብሎም ከሌሎች ዓለማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ከፈለግን ትምህርት ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አስተዋጽኦ ለማስቀጠል እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትምህርት ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ማንንም ሳንጠብቅ ራሳችን በራሳችን መሥራት እንደምንችል ዛሬ የተመረቁት ትምህርት ቤቶች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። ሥራዎችንም በትብብር መሥራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና አልማ በትምህርት ዘርፉ እያደረጉት ላለው አበርክቶም አመሥግነዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እያደረገው ያለውን ሥራ መደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

መማር ማለት የባሕሪ ለውጥ ማምጣት እና ያስተማረን ማኅበረሰብ መልሶ መደገፍ ነው ብለዋል። ያስተማረን ሕዝብ አለመደገፍ ማንነትን መርሳት መኾኑንም ተናግረዋል። በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ወገኖች የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች እንዲደግፉ ጠይቀዋል። ከተባበርን፣ ወደ አንድ ከመጣን እና ወደ ቀልባችን ከተመለስን ሁሉን ማድረግ የሚያስችል አቅም አለን ነው ያሉት።

ያለንን አቅም ተጠቅመን የሀገር ክብር ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል። ሁሉም ለትምህርት ዘርፉ ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ድልድዮች፣ የጌጠኛ መንገድን ጨምሮ 67 ፕሮጀክቶች ናቸው ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት።

ዛሬ የሚመረቁ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄዎች ኾነው የቆዩ ናቸው ተብሏል። በከተማዋ እየተመረቁ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በከተማ አሥተዳደሩ፣ በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ)፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በግለሰቦች እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተገነቡ ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኅዳር 12 በታሪክ”
Next articleየተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መቀነስ እንደተቻለ የኢንፎርሜሽን እና መረብ ደኅንነት አሥተዳደር አስታወቀ፡፡