
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በየዘመኑ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች የሚያደርሱት ጉዳት እንዳለ ኾኖ አስተምረውት የሚያልፉትም ልምድ አለ።
በዘመናት ሂደት በሰው ልጆች ላይ የማይረሳ ጠባሳ እና ልምድ ጥለው ካለፉ በሽታዎች ውስጥ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ አንዱ ነው።
ሽብሩ ተድላ በ2013 ዓ.ም “ወረርሽኝ” በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ እንዳስቀመጡት “ኢንፍሉዌንዛ” እየተባለ የሚጠራው ወረርሽኝ የተከሰተው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1918 (ኅዳር 1911 ዓ.ም) ነው።
በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በጣም የታወቀው በኅዳር ወር 1911 ዓ.ም ስለነበር በማኅበረሰቡ “የኅዳር በሽታ” እያለ ይጠራው ጀመር።
በወረርሽኙ እስከ 40 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሕይዎታቸው እንዳለፈ ይነገራል። አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደነበርም ነው የሚነገረው።
በሽታው በአምራቹ ኀይል ላይ ባደረሰው ጉዳት ከሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት ጥሎ አልፏል።
በወቅቱ በሽታውን ለመከላከል እንደ መፍትሔ የተቀመጠው ደግሞ ቆሻሻን ማስወገድ፣ ማቃጠል እና አካባቢን ማጽዳት አንዱ ነበር።
የጽዳት ሥራው ለተከታታይ ዓመታት የተለያዩ የሽታ አምጭ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደ ባሕል ተወስዶ በየዓመቱ ኅዳር ወር በተለይም ደግሞ ኅዳር 12 ቀን የግል እና የአካባቢ ጽዳት ዘመቻ ይደረግ ነበር።
በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንክር እንዳሉት የአካባቢ ቁጥጥር እና የግል ንጽህና የመተንፈሻ አካላት በሽታ ብቻ ሳይኾን ሌሎች በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል ወሳኝ መፍትሄ ነው።
በተለይም ደግሞ ጉንፋንን ጨምሮ የማኅበረሰብ ጠንቅ እየኾኑ የመጡትን ወባ እና ኮሌራን ለመከላከል የግል እና የአካባቢ ንጽሕና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሌሎች መከላከያዎች እንዳሉ ኾኖ በማኅበረሰቡ አቅም የሚሠሩ ያቆሩ ውኃማ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ ማዳፈን፤ የግቢ እና አካባቢ ንጽህና መጠበቅ ትንኟ እንዳትራባ ስለሚያደርግ በሽታውን ቀድሞ መከላከል ይቻላል።
የመተንፈሻ በሽታዎችን ለመከላከል የግል እና የአካባቢን ንጽሕናን መጠበቅ፣ የኮሌራ በሽታንም የምግብ ንጽሕናን በመጠበቅ እና ውኃን በማፍላት እና በማከም መከላከል ይቻላል ነው ያሉት።
ከተለያዩ በሽታዎች ራስን ለመጠበቅ ለማኅበረሰቡ ስለአካባቢ ንጽሕና በየጊዜው በጤና ባለሙያዎች ትምህርት እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!