
አዲስ አበባ: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጽዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ በየዓመቱ በኅዳር ወር ይካሄዳል። በዚህ ዓመትም ከኅዳር ወር ጀምሮ “ትርክታችን አዲስ አበባችንን ጽዱ ማድረጋችን” በሚል መሪ መልዕክት የጽዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተማ እና ወረዳዎች ተካሂዷል።
የጽዳት ዘመቻውን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየአካባቢው የሚወድቀው ቆሻሻ አካባቢን እንዳይበከል እና የጤና ጠንቅ እንዳይኾን የሚያስችል የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ተዘርግቶ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የጽዳት ዘመቻው ዋና ዓላማ አዲስ አበባን ውብ፣ ጽዱ፣ ማራኪ እና ዘመናዊ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ከባቢ መፍጠር ነው ብለዋል። በተከናወነው ተግባርም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነው ከንቲባዋ የተናገሩት። አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ የጽዳት ዘመቻው በአንድ ወቅት ብቻ የሚከናወን ሳይኾን የዘወትር ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡ ቆሻሻን የመለየት፣ የመሠብሠብ እና የማስወገድ ልማዱ እና ተሳትፎው ከምንጊዜውም በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከንቲባዋ አሳስበዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አሥተዳደር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አዲሱ ሻንቆ አዲስ አበባን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻ እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
አዲስ አበባ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ካሉ ከተሞች ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንድትኾን የተጀመረው የጽዳት ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል። የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች ኅብረተሰቡ ቆሻሻ ሃብት መኾኑን የመረዳት እና በአግባቡ የመሠብሠብ ልማዱ ደካማ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እና ተሳትፎ እያደገ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ቆሻሻን ከማቃጠል ይልቅ በአግባቡ በመሠብሠብ አካባቢው እንዳይበከል እና ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል። በቀጣይ ግንዛቤያቸውን እና ተሳትፏቸውን በማሳደግ ለጤና ተስማሚ እና ንጹህ ከባቢ አየር ከመፍጠር ባሻገር ቆሻሻን ወደ ሃብትነት ለመለወጥ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
በጽዳት ዘመቻው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የከተማው ነዋሪዎች መሳተፋቸውም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!