የህጻናትን መብት በመጠበቅ የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት እንደሚገባ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን አሳሰበ።

35

ሰቆጣ:ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (ዓሚኮ) ኢትዮጵያ የህጻናትን መብት ለማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የህጻናት ቀን “ህጻናት የሚናገሩት አላቸው እናድምጣቸው” በሚል መሪ መልዕክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ እየተከበረ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ዓለም አቀፉን የህጻናት ቀን ስናከብር ለስሙ የተቋቋመ ሳይኾን ህጻናት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እንዲለማመዱ በማድረግ ሀገርን ለመገንባት በማለም ነው ብለዋል።

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 36 ላይ የህጻናትን መብት በአግባቡ እንዳስቀመጠው ሁሉ እኛም በህጻናት እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ልንከላከል ይገባል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው “የህጻናትን መብት በመጠበቅ የነገዋን ኢትዮጵያ ልንገነባ ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የህጻናትን ቀን ለማክበር ከተገኙት መካከል ተማሪ ኤልዳና አቤል ባለፉት ዓመታት የፓርላማ አባል በመኾን ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ በማድረግ በኩል ከመምህራን ጋር ሥትሠራ እንደነበረች ገልጻለች። በቀጣይም መንግሥት ለህጻናት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቀችው።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ የስሃላ ሰየምት ወረዳ ተማሪ ሔለን ወልዳት ከፊታችን በሚመጣው ጥር ወር እድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናት ያላቻ ጋብቻ እና ያለ እድሜ ጋብቻ እንዳይፈጸም መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቃለች። የህጻናት ቀን መከበሩም ለልጆች ልዩ ትርጉም አለው ነው ያለችው።

በሀገራችን የተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት በህጻናት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ እንዳለፈ የተናገሩት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ፈንታ ዓለሙ ሲኾኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና ህጻናት ችግራቸውን ፊት ለፊት እንዲገልጹ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚፈጠሩ የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ እና ጥቃቶችን ለመቅረፍ የፓርላማ አባላትን በመወከል ችግሮቻቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ለማድረግ የተጠናከረ አደረጃጀት እንደፈጠሩ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትቨርህ ታደሰ ገልጸዋል።

ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደው የፓርላማ አባላት ምርጫ ህጻናት በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግርንን እንዲረዱ ያደርጋል ብለዋል። በቀጣይም በቀበሌ፣ በትምህርት ቤቶች እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሥራት በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በጋራ የመከላከል ተግባር ይከወናሉ ብለዋል።

በሀገራችን ለ19ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የህጻናት ቀን በዓል ላይ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከወረዳ የተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የህጻናት የፓርላማ አባላት እና ተማሪዎች ተሳታፊ ኾነዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት የ2017 የከተማዋን በጀት አጸደቀ።
Next articleከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ማኅበረሰብ የተሳተፈበት የጽዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡