
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ከ78ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ እንደተገባ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ የወረኢሉ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ኢክራም ሁሴን ዕድሜዋ 13 ዓመት ሲኾን የ5ተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ተማሪ ኢክራም ጎበዝ ተማሪ እንደኾነች እና ስታድግ መምህር መኾን እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ ተማሪዋ ያሰበችው ደረጃ ላይ ለመድረስ የግድ ሙሉ ጤነኛ መኾን እንዳለባት ነው የገለጸችው።
ለዚህም አሁን የሚሰጠውን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በመከተብ ጤናዋን ጠብቃ በጥሩ ውጤት ለማለፍ እና ቤተሰቦቿን ለማስደሰት ዝግጁ ስለመኾኗም ተናግራለች፡
በዞኑ ለ78 ሺህ ልጃገረዶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ባለው 29 ሺህ 305 የሚኾኑ ልጃገረዶችን ማስከተብ እንደተቻለ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ብርሃን ኀይሉ ገልጸዋል፡፡ ከታቀደው 39 በመቶ የሚኾነውን በሁለት ቀናት ውስጥ ማሳካት እንደቻሉም ነው የተናገሩት፡፡
በቀሪዎቹ ሦሥት ቀናት ውስጥ ቀሪዎቹን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ በስፋት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል፡፡ በዞኑ ሁለት ከተማ አሥተዳደር እና 11 ወረዳዎች ላይ ክትባቱ ከኅዳር 09/2017 ዓ.ም እስከ ኅዳር 14/2017 ዓ.ም በየትምህርት ቤቶች እና በጎጥ ደረጃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ከልጃገረዶች የክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ለኾኑ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ በሁሉም ወረዳዎች እየተሠጠ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በዘመቻው ከ2 ሺህ በላይ የሚኾኑ የጤና ባለሙያዎች እና የአሥተዳደር ሠራተኞች እንደተሳተፉ ተገልጿል፡፡
በዞኑ ከአምስት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ሲሰጥ መቆየቱንም ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
