
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር ከነበረባት የሰላም ችግር እያገገመች ነው፡፡ ከነበረባት የሥጋት ድባብ ወጥታ ወደ ልማቷ እየገባች ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ከቁዘማ ወጥቶ ወደ ሰላማዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሩ ተመልሷል፡፡
የግጭት ድባብ ውስጥ ኾኖም የተሠሩ የልማት ሥራዎንችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል፡፡ በከተማዋ ለአዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችም መሠረት ተጥሏል፡፡ ድልድይ፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መኖሪያ ቤት ተገንብተው መመረቃቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የሚጀመሩ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስታድየም እና የከተማ አስተዳደሩ ህንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ መቀመጥም ሌላኛው የሰላም እና የልማት ነጸብራቆች ናቸው፡፡
ኅብረተሰቡ፣ አመራሩ፣ የመከላከያ እና የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ሰላሙ በሚጸናበት እና ልማት በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ እና በውይይቱ የተሳተፉት በመከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ 302ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መለስ መንግሥቴ ከተማ አሥተዳደሩ በግጭት ቀጣና ውስጥ ኾኖም የልማት ሥራዎች በመሥራቱን አመስግነዋል፡፡ የሰላም፣ የልማት እና ትርፍ አምራች የኾነውን ሰሜን ጎጃም ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር ሰላሙን አውኮት ቆይቷል ብለዋል፡፡ ይሁንና እኛም እናንተም በሥልጡን አስተሳሰብ እየተወያየን፣ ችግሮችን በንግግር እና በሰለጠነ መንገድ እየፈታን ሰላሙን እንመልሰዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስለ አማራ ሕዝብ ልማት የሚያስብ አካል ነፍጥ አንስቶ አይዋጋም ነበር፡፡ የገደሉት፣ ያደኽዩት፣ እንዳይንቀሳቀስ አስረው የያዙት የአማራን ሕዝብ ነው፤ እስካሁንም ድረስ ገንዘብ መሰብሰብ፣ መዝረፍ፣ ሰላሙን መንሳት እንጂ ያተረፉለት ነገር የለም ነው ያሉት፡
ኅብረተሰቡም ሃሳባቸው ገብቶት፣ ግባቸውን ተረድቶ እና የትም እንደማይደርሱ ተገንዝቦ እረፉ ሊላቸው ይገባል፡፡ ትምህርት የከለከሉ፣ ማዳበሪያ የከለከሉ፣ ሕዝብ የማያከብሩ እንዴት የአማራን ጥያቄ እንወክላለን ይላሉ? በማለት ታጣቂው ኃይል መፍትሄ እንደማይኾን አብራርተዋል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል መለስ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲደርስ ያደረገው መከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት እየከፈለ አጅቦ እንጂ ዘራፊው ኃይል አይደለም ነው ያሉት፡፡ አሁን የሚታየው ጥሩ የሰብል ቁመና በመከላከያ ጥበቃ በቀረበ ማዳበሪያ የተዘራ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ኅብረተሰቡም በተለይም አባቶች ይህንን ተገንዝባችሁ ጫካ ወጥተው ሰላም የሚነሱ እና የሚያወድሙ ኃይሎችን በመምከር እና በመቆጣት ከጥፋታቸው እንዲመለሱ ልታደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም ኾኑ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ይህንን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላም እንዲገቡ አባቶች ልትቆጡ እና ልትመክሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል መለስ “የሰላምን ጥቅም የምታውቁ ሁሉ ልጆቻችሁን ምከሩ”ብለዋል፡፡ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነት እንዳይጀመር፤ ከተጀመረ በኋላም እንዲቆም ያደረገውን ጥረት አስታውሰው ጦርነቱ በመደረጉ የበለጠ የተጎዳው ሰላማዊው አርሶ አደር እና የታችኛው ኅብረተሰብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አሁንም በአማራ ክልልም ተጨማሪ ጥፋት ሳይከተል ለሰላም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር አመራሮች በቀውስ ውስጥም ኾነው ተስፋ ባለመቁረጥ በብሩሕ ተስፋ ልማትን በመጀመራቸው አመስግነዋል፡፡ ኅብረተሰቡም አመራሮቹን ሊደግፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ አማራሩ በንጽህና እና በትህትና ኅብረተሰቡን በማገልገል ልማቱን የበለጠ እንድያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
