
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ/ም (አሚኮ) እንደ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለማርገብ የሰላም ማስከበር ሥራው በትኩረት መከናዎኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎች ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ከማድረግ ባሻገር ደህንነቷን በዘመናዊ ካሜራዎች ለማስጠበቅ ሥራዎች ተጀምረዋል ብለዋል። ኀብረተሰቡን የመፍትሔው አካል በማድረግም ሰላሙ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።
እንደ ክልል አጋጥሞ በነበረው የጸጥታ ችገር ምክንያት በባሕር ዳር ከተማም 23 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ትምህርት አቋርጠው እንደነበር አቶ ጎሹ አስታውሰዋል። አሁን ላይ ግን ሰላም በመስፈኑ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ ናቸው ነው ያሉት። በ2016 በጀት ዓመት በችግር ውስጥ ኾኖም ለ62 ሺህ 251 በከተማ እና በገጠር ለሚኖሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አቶ ጎሹ አንስተዋል። በአንድ በኩል ጸጥታውን እያስጠበቅን በሌላ በኩል ልማቱን እያስቀጠልን ነው ብለዋል።
ከመሬት የሊዝ ጨረታ 281 ሚሊዮን 9 መቶ 59 ሺህ 684 ብር ተገኝቷልም ብለዋል። የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታትም ጥረት ተደርጓል ያሉት አቶ ጎሹ ከ14 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የመሥሪያ ቦታ እንደተሰጠ ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ከተማ አሥተዳደሩ የጠጠር፣ የአስፋልት እና የጌጠኛ መንገድ ሥራዎች መገንባቱን አቶ ጎሹ በስኬትነት አንስተዋል። በሁሉም የባሕር ዳር ክፍለ ከተሞች 80 ሄክታር መሬት ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አሰታውሰዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የምክር ቤት አባል ወይዘሮ መብራት ይርሳው በችግር ውስጥ ኾነን ልማቱን ማስቀጠላችንን እንደ ስኬት አይቸዋለሁ፤ የመሠረተ ልማቱ ሥራም ይበረታታል ነው ያሉት።
ከጭስ ዓባይ ከተማ የተወከሉት የምክር ቤት አባል አቶ በቀለ ዘሬ በጭስ ዓባይ ከተማ ልማታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል። ወቅታዊው የጸጥታ ችግር በርካታ ሥራዎችን አስቀርቶብናል። የአሁኑ ጅምር ግን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
