
ጎንደር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ግብዓት የማሠባሠብ መድረክ በጎንደር እያካሄደ ነው።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የቢሮ ኀላፊዎች፣ ከንቲባዎች፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እንዲኹም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ጎንደር የኪነጥበብ፣ የኪነ ሕንጻ እና የኪነ ውበት አድባር ናት ብለዋል። አድባር በኾነች ከተማ በሕግ ማዕቀፎች ለመወያየት ስለተገናኘን አመሠግናለሁ ነው ያሉት።
በዓለም ደረጃ የከተሜነት ማስፋፋት እያደገ እና ትልቅ አጀንዳ እየኾነ መጥቷል ያሉት ኀላፊው የከተሜነት መስፋፋት በክልሉ የራሱ የኾነ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል። ከተሜነት ሲያድግ ኢኮኖሚ አብሮ እንደሚያድግም ገልጸዋል። ከተሜነት በአግባቡ ካልተመራ የራሱ የኾነ ችግር እና አደጋ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በትልልቅ ከተሞች የሥራ እንቅስቃሴ ዕድገት እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል። የሥራ እንቅስቃሴ እና የአሥተዳደር ለውጦችም እንደሚካሄዱ ነው ያነሱት። በከተሞች ቤት እና መንገድ ሢሠራ ሲፈርስ እንመለከታለን ያሉት ኀላፊው ከተሞችን በአግባቡ መምራት እና ማሥተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል። ከተሞችን በአግባቡ ለመምራት ደግሞ የተቋም ግንባታ በእጀጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የተቋም ግንባታ ሥራ የሰው ኀይል፣ የቴክኖሎጂ እና የአሠራር የሕግ ማዕቀፍ ሥራዎች መኾናቸውንም ነው ያመላከቱት። የከተማ ልማት እና ዕድገትን ለማስተካከል፣ ችግሮችን አርሞ የወደፊቱን ዘመን የዋጁ ከተሞችን ለመገንባት የአሠራር ሥርዓቶች እና የሕግ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉ አስገንዝበዋል።
በውይይቱ የሚነሱት አጀንዳዎች ለከተማዎች ወሳኝ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የከተማ ገቢ እና የከተማ የቤት ልማት ስትራቴጂዎች እንደሚመከርባቸው ገልጸዋል። ከተሞች ገቢያቸውን በአግባቡ መሠብሠብ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። ከተሞች ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እና ፍትሐዊ እንዲኾኑ የተዘጋጀ የአሠራር ሥርዓት መኖሩንም ገልጸዋል።
በክልሉ የቤት ልማት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። ችግሮችን ለመፍታት እና በቀጣይ የከተሞችን ዝግጁነት ማሳየት የሚያስችል ስትራቴጂ ማዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ስትራቴጂዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ገንቢ ሃሳቦችን እንዲያነሱም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
