የኢንተርኔት አሥተዳደር ሥርዓቱን ደኅንነት የሚያስጠብቁ አዋጆች እና የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ የሕዝብ ተወካዩች ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቆመ።

44

አዲስ አበባ: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 13ኛው የአፍሪካ የኢንተርኔት አሥተዳደር ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ነገሬ ሌንጮ (ዶ.ር) ምክር ቤቱ አሠራርን የሚያሳልጡ መመሪያዎችን፣ አዋጆችን እና ሕጎችን በማውጣት እንዲተገበር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ጨምሮ የዳታ ደኅንነት ጥበቃ አሥተዳደር እንዲሁም ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን ማጽደቁንም ተናግረዋል።

እንደ አሕጉር በዲጂታል ዘርፉ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ ፖሊሲ ክፍል ኀላፊ አዲል ሱሌይማን በአፍሪካ ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት አሥተዳደር ለመገንባት ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አህጉሪቱ እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያሉ ከፍተኛ የኢንተርኔት መሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።

ፎረሙ ለተከታታይ ሦሥት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እናንተ ሁላችሁ የጎንደር ከንቲባዎች ናችሁ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
Next article“ከተሞችን በአግባቡ መምራት እና ማሥተዳደር ያስፈልጋል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)