“እናንተ ሁላችሁ የጎንደር ከንቲባዎች ናችሁ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

73

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ግብዓት የማሰባሰብ መድረክ በጎንደር እያካሄደ ነው።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የቢሮ ኀላፊዎች፣ ከንቲባዎች፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር ከከንቲባነት እሳቤ ጋር የረጅም ዘመን የታሪክ ቁርኝት ያላት ከተማ ናት ብለዋል። ከንቲባ ለጎንደር ሹም የሚሰጥ ማዕረግ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ ነው ያሉት። በሌላ ቋንቋ “እናንተ ሁላችሁ የጎንደር ከንቲባዎች ናችሁ” ብለዋል።

ጎንደር የከተሜነት መገለጫ ተደርጋ ስትወሰድ መኖሯንም ተናግረዋል። መልካም ሀገር ጎንደር የምትባለው መዲና በታሪክ ሊቃውንት ዘንድ የአፍሪካ ካሚሎት (የአፍሪካ መናገሻ) የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል ነው ያሉት። የስልጣኔዋ መገለጫ ሁሉን አቀፍ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዛሬ ቅርስ የሚል የክብር ስም ያጎናጸፍናቸው የጎንደር አሻራዎች ትናንት የከተመችበት የግንባታ ልማት ነበሩ ብለዋል።

ጎንደር የጥበብ፣ የዕውቀት፣ የኪነት እና የንግድ ማዕከልም ናት ነው ያሉት። ያንን ዘመኗን ዳግም ለመመለስ እየሠራን ባለንበት ወቅት ወደ ከተማችን በመምጣታችሁ ደስ ብሎናል ብለዋቸዋል እንግዶችን። ኢትዮጵያ እንደ አክሱም ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ፣ እንደ ሀረር የረቂቁ፣ እንደ ላሊበላ በዓለት ሥልጣኔ የፈኩ፣ እንደ ጎንደር በከተሜነት ያበቡ አያሌ ከተሞች ነበሯት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያንን ጥንታዊ ሥልጣኔ ተከታትሎ አልቀጠለም፣ እርስ በእርስ አልተማማርንም፣ መልካም ልምድ አልተከፋፈልንም ነው ያሉት።

በየራሳችን ጥግ ይዘን ከተሞቻችንን ከዓለም በመነጠል አንዳችን ከሌላው እንዳንማር በር ዘግተን ኖረናል ብለዋል። በአንድ ሀገር የአንድ ከተማ እድገት ብቻውን ውድቀት እንጂ ስኬት አለመኾኑንም ተናግረዋል። “ሁላችንም ስለ ሁሉም ከተሞቻችን አስበን ከሠራን አብረን እንቆማለን፣ አብረን እንለማለን፣ ውጤቱም የበለፀጉ ከተሞች ባለቤት አድርጎ ሕልማችንን እውን ያደርጋል” ብለዋል።

ታሪካዊት ከተማችንን ወደ ቀደመ ክብሯ የሚመልስ ብልጽግና ወጥነንላታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያን በማሳካቱ ሂደት የሁላችንም አብሮነት ያስፈልጋል ነው ያሉት። እኛ ጋር የሌሉ እናንተ የበቃችሁባቸውን ዕውቀቶች፣ አሠራ እና ስልት ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አለን ብለዋል። እኛ አለን የምንለውን እና ለከተሞቻችሁ የሚጠቅመውን ልምድ ልናጋራችሁ ዝግጁ ነን፤ ከዚያም ሲያልፍ ግዴታችን ነው፣ ከተሞቻችሁ የእኛም ከተማ ናቸው ነው ያሉት።

ከተማችን ጎንደርም የእናንተ ከተማ ናት ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንኳን ወደ ራሳችሁ ከተማ በደህና መጣችሁም ብለዋቸዋል እንግዶችን።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕጻናት መብቶቻቸውን በሚገባ እንዲያውቁ ምቹ ኹኔታ መፍጠር ይገባል።
Next articleየኢንተርኔት አሥተዳደር ሥርዓቱን ደኅንነት የሚያስጠብቁ አዋጆች እና የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ የሕዝብ ተወካዩች ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቆመ።