ሕጻናት መብቶቻቸውን በሚገባ እንዲያውቁ ምቹ ኹኔታ መፍጠር ይገባል።

19

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሕጻናት የሚሉት አላቸው እናድምጣቸው” በሚል መሪ መልዕክት በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕጻናትን መብት ሊያስከብር የሚችል ሀገራዊ ፖሊሲ እና ፕሮግራም በመቅረጽ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ይህን ቀን ከወላጅ ጀምሮ ሁሉም ማኅበረሰብ ለሕጻናት የሚበጅ ነገር ለማድረግ ትልቅ ንቅናቄ የሚፈጥርበት ቀን መኾን እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ሕጻናት መብቶቻቸውን በሚገባ እንዲያውቁ እና ድምጻቸው እንዲሰማ ምቹ ኹኔታ የሚፈጠርበት ጊዜ ይኾናልም ብለዋል።

ሀገር ለልጆቿ ማድረግ የሚገባትን ለማድረግ መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር እየመከረ እንደሚገኝም ታውቋል።

በተለያዩ ግጭቶች ተጎጂ ለኾኑ ሕጻናት ትኩረት በመስጠት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ ነው ብለዋል ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ።

ሚኒስትሯ ሕጻናትን በማድመጥ መብታቸው እንዲከበር መንግሥት እና የተለያዩ አደረጃጀቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ለሕጻናቱ አስተላልፈዋል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ በመርሐ ግብሩ ላይ ሀገር አቀፍ የሕጻናት ፖርላማ አፈ ጉባኤ ሕጻን ቅዱስ ሙላትን ጨምሮ በርካታ ሕጻናት ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሲቃኝ!
Next article“እናንተ ሁላችሁ የጎንደር ከንቲባዎች ናችሁ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው