የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሲቃኝ!

86

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቀይ ባሕር  በእስያ እና በአፍሪካ መካከል የተዘረጋ ሰፊ ባሕር ነው፡፡ ስፋቱ 438 ሺህ ኪሎ ሜትር ይደርሳል። ወደ ታች ጥልቀቱ በአማካኝ 490 ሜትር ቢኾንም ከፍተኛው እስከ 3 ሺህ 40 ሜትር ይጠልቃል።

በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ እንደኾነ የሚነገርለት ቀይ ባሕር ነጃጅ፣ ድኝ እና ሳልፉር የመሳሰሉ ማዕድናትን አቅፎ ይዟል። 1 ሺህ 2ዐዐ የዓሳ ዝርያዎችም አሉት። ከእነዚህ የዓሳ ዝርያዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚኾኑት በሌላ አካባቢ የማይገኙ ናቸው።

አካባቢው ባለው መልካምድራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ምቹነት የተነሳ የትኩረት ማዕከል ነው። ከቅርብም ከሩቅም ያሉ ሀገራት የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ምህዋር እና የወታደራዊ የጦር መንደር መመስረቻ አድርገውታል። በቀጣናው 11 ሀገራት የጦር ኀይል መንደር አቋቁመዋል። ከእነዚህ ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ቱርክ ተጠቃሽ ናቸው። 

ቀይ ባሕር ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታው እጅግ በጣም የጎላ ነው። በዓለማችን ከሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚኾነው የሚጓጓዘው በዚሁ መስመር ነው። በርካታ ሀገራት በየዓመቱ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠሩ ሸቀጦችን ያመላልሱበታል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ደግሞ እጅግ ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ የወደብ አገልግሎትን ይጠቀማሉ።

ኢትዮጵያ ባላት ፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት፣ ከተለያዩ ሀገራት ጋር እያደረገቻቸው ባለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሚፈጠሩ የንግድ ግንኙነቶች ማደግ፣ ባላትየማደግ ፍላጎት እና ባላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ምክንያት አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ ነው።

በመኾኑም ኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጮችን ማማተር ግድ ብሏታል። ለዛም ነው ከተለያዩ ሙከራዎች በኋላ በቅርቡ ወደ ሶማሊላንድ ፊቷን ማዞሯ ። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ኢትዮጵያን የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የማደግ ፍላጎት እና ያላትን ለውጥ ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ የሚኖረው ሚና ትልቅ ነው።  የነገዋን ትልቋን ኢትዮጵያ ለማየት መሠረት የሚጥል ቁልፍ የለውጥ መሰላልም ተደርጎ ይወሰዳል።

በዓለማችን 43 የሚደርሱ ሀገራት ምንም ዓይነት የባሕር በር አማራጭ የላቸውም። ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ 32 የሚኾኑት ታዳጊ ሀገራት ናቸው ። በአፍሪካ ስንመለከት ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 ሀገራት የባሕር በር የላቸውም።

እንደ ውቅያኖስ እና ባሕር ያሉ ትላልቅ ውኃማ አካላት የሁሉም የዓለም ሕዝብ ሃብቶች ተደርገው የሚታዩ እና ከእነዚህ ውኃማ አካላት የሚገኘውን ጥቅም ማንኛውም ሀገር የማግኘት መብት እንዳለው የሚደነግግ ዓለም አቀፍ ሕግ አለ። ይህ ሕግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ ስምምነት (UN Convention on Law of Sea) የሚባል ሰነድ ነው።

በዚህ ሰነድ አንቀጽ 86 እና 87 ላይ በየብስ የተዘጉ ሀገራትም ይሁኑ ለባሕር ክፍት የኾኑ ሀገራት ትላልቅ የውኃማ አካላት ላይ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

ሰነዱ በአንቀጽ 125 ከ1 እስከ 3 በዘረዘራቸው ነጥቦች ላይ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር መዳረሻ በኾኑ ሀገራት ተጉዘው ከባሕር ሊገኝ የሚችለውን የባሕር በር አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ እና ይህ ሲኾን ግን ባሕር ለመድረስ የሚያቋርጡት ሀገር ጋር ስምምነቶችን ማድረግ እንዲሁም የዛን ሀገር ሉዓላዊነት በማክበር ሊኾን እንደሚገባ ያስረዳል።

ዓለም አቀፍ ድንጋጌው አንድ ሀገር የሌሎችን ሀገራት ድንበር ሁሉንም ዓይነት የመጓጓዣ መንገዶች በመጠቀም የመሸጋገር ነፃነትን የሚሰጥ እና ለባሕር ዝግ የኾኑ ሀገራት ከውኃማ አካላት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል እንደኾነ የገለጹልን የዓለም አቀፍ ሕግ መምህሩ ዘውዱ መንገሻ የአንድን ሌላ ሀገር ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ አልፎ የወደብ ግልጋሎት የሚያገኝ ሀገር ከሚሰጠው ሀገር ጋር ስምምነት ማድረግ እንዲሁም ሕጋዊ ጥቅሞቻቸው እንዳይነኩ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ለ50 ዓመት የሚቆየው የባሕር በር ስምምነት ሀገሪቱ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ያላት መኾኑ፣ በወደብ ክፍያ ብቻ ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግ መሞከር ያለውን ኪሳራ በማሰብ፣ እያደገ የመጣውን የውጭ ንግድ ለማሳለጥ ባሕር ጋር መድረስ ወሳኝ በመኾኑ ከምን ጊዜውም በላይ የባሕር በር ጥያቄ ከምክንያት በላይ ተደርጎ መታየት የሚችል ነው።

ወደብ አልባ ሀገራት ዓለም አቀፍ መርሕን እና ሕግን ተከትለው የባሕር በር ለማግኘት ከቻሉ ፍትሃዊ እና የመልማት ፍላጎትን ዕውን ለማድረግ የተደረገ ሂደት ተደርጎ የሚቆጠር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካ እና መልካ ምድራዊ ፍላጎቶች ጎልተው በሚታዩበት ቀጣና በጋራ መጠቀም የሚያስችሉ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መረጋጋት እና ማደግ ሰላም የማይሰጣቸው አካላት ምቾት የነሳቸው ጉዳይ ኾኗል። በመኾኑም ውጤታማ ለመኾን የዓለም አቀፍ ሕግን እና የተጠና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የተከተለ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ ተስፋዎች ዕውን እንዲኾኑ እና ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነቷ ውጤታማ እንዲኾን ዓለም አቀፍ የሕግ መሠረቶች ላይ ተመሥርቶ መዝለቅ፣ ዲፕሎማሲን ማጠናከር፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ግጭቶችን ለሀገር በሚጠቅም መልኩ እንዲፈቱ ማድረግ እና ውስጣዊ አንድነትን ማሳደግ እንደሚገባ መምህሩ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ከ194 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው።
Next articleሕጻናት መብቶቻቸውን በሚገባ እንዲያውቁ ምቹ ኹኔታ መፍጠር ይገባል።