
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን 194 ሺህ 390 ልጃገረዶች ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዞኑ ጤና መምሪያ የክትባት ክፍል ባለሙያ በላይ አምባቸው ገልጸዋል። እስከ አሁንም በዞኑ ከሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ ግብዓት በገባባቸው ደራ፣ እብናት እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ከኅዳር 10/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክትባቱ እየተሠጠ ይገኛል።
በ11 ወረዳዎችም በሁለት ቀጣናዎች ግብዓት እየተጓጓዘ ይገኛል። ከኅዳር 12/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክትባቱ የሚሰጥ ይኾናል ብለዋል ባለሙያው። ግብዓቱ ዘገይቶ በገባባቸው አካባቢዎች ክትባቱ ከተጀመረ ጀምሮ ባሉ አምስት ተከታታይ ቀናት ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ክትባቱን በትምህርት ቤቶች፣ ቤት ለቤት እና በሌሎች አማራጮች ይሰጣል።
ወላጆች እና ተቋማት መከተብ የሚገባቸውን ልጃገረዶች እና በክትባት ወቅት ያለፋቸው ልጃገረዶች እንኳ ቢኖሩ በሌሎች ክትባት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ተገኝተው እንዲወስዱ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዞኑ ከማህጸን በር ካንሰር ጎን ለጎን የህጻናት የምግብ እጥረት ልየታ፣ ያልተከተቡ ህጻናት መከተብ እና ሌሎች ሥራዎችም እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
