“በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

48

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ሌሎች የክልሉና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የሥራ ኀላፊዎቹ የዓባይ ጋርመንት ፋብሪካን እና የቲቲኬ ኢንዱስትሪን ነው የጎበኙት። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በጎንደር ከተማ የተመለከቷቸው ፋብሪካዎች ለማኅበረሰቡ ምርትን በማቅረብ እና የውጭ ምንዛሬን በማምጣት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው የተናገሩት። የኢንዱስትሪዎችን ማነቆ ለመፍታት በርካታ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። የኀይል እጥረት እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት መሠራቱን እና ወደፊትም እንደሚሠራ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት እና በዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት ምጣኔ እየጨመረ መኾኑን ተናግረዋል። ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። ለኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር እየተፈጠረ መኾኑን ነው የተናገሩት። ኢንቨስትመንት ሰላም ይፈልጋል ያሉት ኀላፊው ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ሰላም ያስፈልጋል፣ ይህ እንዲኾን ደግሞ ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባዋል ነው ያሉት።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ማድረጉን አንስተዋል። ይህ ደግሞ የሥራ እድል በመፍጠር በኩል ተጽዕኖ አሳድሯል ነው ያሉት።

ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሰላሙን እያረጋገጠ፣ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እና የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

መሪዎች ኢንዱስትሪዎችን በመከታተል ማነቆዎቻቸውን መፍታት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዞን ያላመዱ እጆች”
Next articleበደቡብ ጎንደር ዞን ከ194 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው።