“አዞን ያላመዱ እጆች”

100

አዲስ አበባ: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ )በተፈጠሮ ሃብት የታደለችው፣ በተንጣለሉት የጫሞ እና ዓባያ ሐይቆች የታቀፈችው፣ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ጫካ እና አንስሳት ቱሩፋቶችን የምትጋራው አርባ ምንጭ ከተማ ዘንድሮ 19ኛውን የብሔር ብሔረሠቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ልታከብር ዝግጅቷን አጠናቅቃለች።

የአርባ ምንጭ አዞዎች በዓባያ እና ጫሞ ሐይቆች ውስጥ ብቻ የሚገኙ አይደሉም። አዞን እንደ ዓሳ አላምዶ በገንዳ ውስጥ በሰዎች እንክብካቤ ይራባሉም እንጂ። በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው እና በ1976 ዓ.ም ተቋቁሞ በ1982 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የአዞ ማራቢያ (ራንች) አሁንም ድረስ በአግባቡ ቀጥሎ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው። በአፍሪካ ካሉ የአዞ ዝርያዎች መካከል አንዱ የኾነው ኮሮኮዳይል በአርባ ምንጭ ይገኛል።

አስደሳች ዳንኤል በአዞ ራንቹ አስጎብኝ ነው። ተቋሙ ለምርምር፣ ለውጭ ገንዘብ ግኝት እና ዝርያ ጥበቃ የተቋቋመ ነው ብለዋል። የአዞ ቆዳ ለውድ አልባሳት መሥሪያነት ያገለግላል። ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ እና የመሳሰሉት ይሠሩበታል። የአንድ አዞ እድሜ አስከ 140 ዓመት ድረስ ይዘልቃል። በአርባ ምንጭ ራንች ውስጥ 36 ዓመታት ገደማ የኾናቸው ትልልቅ ሴት እና ወንድ አዞዎች እንዳሉ አስጎብኝው ነግሮናል።

አንዲት እናት አዞ እንቁላል የምትጥለው በዓመት አንዴ ሲኾን ከ30 አስከ 70 አንቁላል ትጥላለች፤ በዋናነትም ታህሳስ አካባቢ ይጥላሉ። አዞዎቹን የሚንከባከቧቸው እና የሚመግቧቸው ሰዎች አሏቸው። “አዞን ያላመዱ እጆች” እነዚህ ናቸው።

ይህን ስፍራ በወር እስከ 300 የሚደርሱ ጎብኝዎች እንደሚመለከቱት አስጎብኛችን ገልጾልናል። ከዚህ በፊት አዞዎችን ወደ ውጭ ይልኩ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን እየቀነሰ እንደመጣ ገልጿል። የቆዳ አልባሳት የሚያመርቱ አካለት ትኩረት ቢሰጡት ለእነርሱም ለአዞ ራንቹም ጠቃሚ ነው ሲሉ አስጎብኝው ጠቁመውናል።

የአርባ ምንጭ አዞ ራንች ለ36 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ዘጋበ:- አንዱዓለም መናን-ከአርባ ምንጭ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ64 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ገለጸ።
Next article“በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)