
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ኡስማን አሊ እንደገለጹት ክትባቱ በአሥተዳደሩ ውስጥ ለሚገኙ 64 ሺህ 868 ልጃገረዶች ይሰጣል። የክትባት አገልግሎቱ በአምስቱ ወረዳዎች እና በአራቱም ከተማ አሥተዳደሮች እየተሰጠ ነው።
ከ64 ሺህ 868 ልጃገረዶች ውስጥ ከ53 ሺህ በላይ የሚኾኑትን በትምህርት ቤቶች፣ ቀሪዎቹን ደግሞ ከትምህርት ቤት ውጭ ክትባቱን ለማዳረስ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል። እስካኹንም የእቅዳቸውን 24 በመቶ እንዳከናወኑም ገልጸዋል።
ልጃገረዶችን ከማህጸን በር ካንሠር መከላከል ጤናማ ዜጋን የመፍጠር ሥራ ነው ያሉት መመሪያ ኀላፊው እቅዳቸውን ለማሳካትም ከ230 በላይ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን እንዲሰጡ አሰማርተዋል።
መምሪያ ኀላፊው ቀደም ባሉት ሳምንታት ለልጃገረዶች እና ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሠራታችው ክትባቱን ለመስጠት ምንም አይነት ችግር አላጋጠመንም ብለዋል።
ከልጃገረዶች ክትባት ጎን ለጎን እናቶችም የማህጸን በር ካንሠር ቅድመ ልየታ በጤና ጣቢያዎች እንዲያደርጉ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
