
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከ27 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃ ገረዶች የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ለመስጠት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ስማቸው ግደይ የማህጸን በር ካንሰር ክትባቱ በዞኑ ለሚገኙ 4 የገጠር ወረዳ እና 5 የከተማ አሥተዳደሮችን ያዳርሳል ብለዋል።
ለዚህም 85 የክትባት ቡድን እንደተዋቀረ ነው የተናገሩት። በቅድመ መከላከል የማህጸን በር ካንሰር ክትባቱ 27 ሺህ 878 ልጃ ገረዶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታሰበም አብራርተዋል።
ምክትል መምሪያ ኀላፊው ስማቸው ግደይ “የክትባት ዘመቻው ውጤታማ እንዲኾን ሆስፒታሎች እና የተመረጡ የጤና ተቋማት የማህጸን በር ካንሰር ልየታው ላይ እየተረባረቡ ነው” ብለዋል።
ቀድሞ የተሠራው የግንዛቤ ሥራ እና የትምህርት ተቋማት በሥራ ላይ መኾን የክትባት ዘመቻውን ውጤታማ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የማህጸን በር ካንሰር ብቸኛው መፍትሄ የቅድመ መከላከል ክትባት ነው። በአማራ ክልል በክትባት ዘመቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ልጃገረዶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይኾናሉ ተብሎም ይታሰባል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
